አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ጥቅም ላይ ያልዋለው የወለጋ ዞን መአድን ሀብት

ጥቅም ላይ ያልዋለው የወለጋ ዞን መአድን ሀብት
ጥቅም ላይ ያልዋለው የወለጋ ዞን መአድን ሀብት

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ አራቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ አንዱ ሆሮ ጉድሩ ነው። እንደሌሎቹ የወለጋ ዞኖች ሁሉ ይህ ዞን የተፈጥሮ ሀብት አብዝቶ ቸሮታል። አየሩም ተስማሚ ነው። ጥቅጥቅ ያሉት ደኖቹም የበርካታ አእዋፋትና የዱር አራዊቶች መጠለያ ናቸው። ይህ የተፈጥሮ ሀብት የአካባቢውን ስነ ምህዳር ሚዛን በመጠበቅ ረገድም ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ከዚህ በዘለለ ታዲያ ዞኑ በውስጡ በርካታ የከበሩና ከፊል የከበሩ መአድናትንም አቅፏል። ለግንባታና ለኢንዱስትሪ ግብአትነት የሚውሉ መአድናትም በዞኑ እንደልብ እንደሚገኙ ይነገራል።

ወርቅን ጨምሮ የድንጋይ ከሰል፣ ኤመራልድና የብረት መአድን ሰፊ ክምችት እንዳለም በጥናት ተረጋግጧል። ይሁንና ለግንባታ ግብአትነት ከሚውሉት ውጪ በተለያዩ ምክንያቶች እነዚህ መአድናት ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም።

የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን መአድን ልማት ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መኮንን ኪቲሳ እንደሚገልፁትም፣ በዞኑ ሰፊ የመአድን ሀብት ክምችት እንዳለ ቢነገርም በዋናነት ግን የብረት፣ የድንጋይ ከሰልና ኤመራልድ መአድናት በተለያዩ ወረዳዎች ላይ እንደሚገኙ በጥናት ተረጋግጧል።

የድንጋይ ከሰልና ኤመራልድ በአሙሩ ጃርቴ ወረዳ እንዲሁም ብረት በአቤ ደንጎሮ ወረዳ ውስጥ እንደሚገኝም ተረጋግጧል። በቀጣይ አውጥቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ተስፋ የተጣላባቸው መአድናትም እነዚሁ ናቸው።

እነዚህ መአድናት በዞኑ እንደሚገኙ በጥናት የተረጋገጠ ቢሆንም ሁሉም መአድናት ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደሉም።ለዚህ ደግሞ በአካባቢ ያለው የፀጥታ ችግር ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።

ችግሩ ባለሃብቶች ወደ ቦታው ደፍሮ በመግባት መአድኑን ለማውጣት እንዲሰጉ አድርጋቸዋል።ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ ባለሃብቶች ቦታው ድረስ መጥተው በማየት መአድኖቹን ለማውጣት በፌዴራል ደረጃ ፍቃድ እየጠየቁ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ማአድናት ውጪ በአሙሩ ጃርቴ ወረዳ ላይ ወርቅ ለማውጣት ፍላጎት ያሳዩ ባለሃብትችም የሚገኙ ሲሆን ከዞኑ አስተዳደርና ከመአድን ልማት ፅህፈት ቤቱ ለባለህብቶቹ የድጋፍ ደብዳቤዎች ተፅፎላቸዋል።

በቀጣዩ የ2014 በጀት ዓመት መአድኑን ጥቅም ላይ ለማዋል ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችም አሉ፡ባለሃብቶቹም ፍቃድ አግኝተው ወደ መአድን ማውጣት ስራው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሂደትም በጂፕሰምና በሌሎች የኢንዱስትሪ መአድናት ውስጥ ባለሃብቶች ገብተው ይሳራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በስፋት የሚመረቱና ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ መአድናትም ይገኛሉ።ከእነዚህ ውስጥም አሸዋ፣ ጥቁር ድንጋይና ጠጠር በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን በማህበር ለተደራጁ በርካታ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረዋል።

በዚህ በጀት ዓመትም ከ2 ሺ 650 በላይ ለሚሆኑና በአነስተኛ ደረጃ በማህር ተደራጅተው የኮንስትራክሽን ማአድናትን ለሚያመርቱ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል።

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፣ መንግስት በዞኑ ከፍተኛ ትኩረት ስጥቶ እየሰራበት ያለው የፀጥታ ጉዳይ ሲሆን በዚህም የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ በመረጋገጡ ወደ ዞኑ ገብቶ በመአድን ልማት ስራ ለመሳተፍ የሚያሳስብ ጉዳይ የለም።

ከመአድን ዘርፍ ጋር በተያያዘ በሁሉም ባለድርሻ አካላትና በህዝቡ በኩል ያለው አመለካከትም እየተቀየረ መጥቷል። በዞኑ የመአድን ልማት ፅህፈት ቤት በኩልም የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በተለይ ባለሀብቶች ወደ ዞኑ ገብተው እንዲያለሙ የማናቃቃት ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በቀጣይም በዞኑ ያለውን የመአድን ሃብት ጥቅም ላይ በስፋት ለማዋል በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች ላይ በጉዳዩ ላይ የሚመክሩ ምክር ቤቶች እየተቋቋሙ ይገኛሉ። በወረዳውም ጂኦሎጂስቶች እንዲቀጠሩ በማድረግ የሰው ሀብት ልማት እንዲሟላ እየተደረገ ነው። ብክንት እንዳይኖርም ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመሆን በተናበበ መልኩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።

በ2014 በመአድን ዘርፉ በርካታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ይጠበቃል።ከዚህ ባለፈ በዘንድሮው በጀት አመት በመአድን ዘርፍ እንደ ዞን በርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ በስፋት ይሰራል።

የመአድን ፍለጋ ለማከናወንም እቅድ ተይዛል።በዚህም 40 ኪሎሜትር ስኩዌር ስፋት ያለውና ወደ ሰባት የሚጠጉ የመአድን አይነቶችን ለመፈለግ እቅድ ተይዟል።

ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 36 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት የሚሸፍን ቦታ በጂኦሎጂስቶች ፍለጋ ለማድረግም ታስቧል። በጥናት ከተረጋገጡት የድንጋይ ከሰል፣ የብረትና የኤመራልድ መአድናት በተጨማሪም ሌሎችንም መአድናት በዞኑ ለማግኘት ፍለጋው በቀጣይ ይካሄዳል።

በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ላይ የድንጋይ ከሰል፣ኤመራልድና ብረት መአድን እንደሚገኝ በጥናት ተረጋግጧል፤

ካርታ ምንጭ፡- የኦሮሚያ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ እ.ኤ.አ 2016

(ኢዜኣ – አስናቀ ፀጋዬ)

Related Post