አርእስተ ዜና
Wed. Nov 13th, 2024

የዘመናችን የፈጠራ ፅሁፎች መንፈስ ምን መምሰል ነበረበት?

የዘመናችን የፈጠራ ፅሁፎች መንፈስ ምን መምሰል ነበረበት?
የዘመናችን የፈጠራ ፅሁፎች መንፈስ ምን መምሰል ነበረበት?

በመኮንን ተሾመ ቶሌራ – በአለማቀፋዊዉ የስነ­ፅሁፍ ታሪክ ዉስጥ የፈጠራ ስራዎች በጣም የተዳከሙበት ዘመናትን “የጨለማዉ ዘመናት” ተብለዉ ይጠራሉ። እነዚህ ግዚያት የሚሸፍኑት የምዕራብ የሮማ ኢምፓዬር ከወደቀበት ከ 500 ዓ∙ዓ∙ እሰከ 14ኛዉ ክፍለ ዘመን “የህዳሴ” ወቅት እስከጀመረበት ያለዉን ወደ አንደ ሺህ መታትን የሚሸፍን ነዉ። ብዙዎች እነዚህን ዘመናት የኢከኖሚ ፣ የባህል እንቅስቃሴዎችና ስነ­ፅሁፍ በጣም የተዳከሙበት ወይም የጠፋበት ጊዜ እንደሆነ ሲናገሩ ሌሎች ደሞ የጨለማ ዘመን ያን ያህል የጨለመ እንዳልነበረ እና የተለያዩ ስራዎችም የተሰሩበት ወቅትም እንደነበረ ይከራከራሉ።

በሀገራችንም እንደዚሁ በጦርነትና በተለያዩ አለም ዓቀፍ ሁኔታዎች ምክንያት በተለያዩ ዘመናት ስነ­ፅሁፍ መቀዛቀዝ የታየባቸዉ ጌዚያት የግእዝ እና የአማርኛ ስነ­ፅሁፍ “የጨለማ ዘመን” እየተባሉ የሚጠሩነትም ጊዜዓት አሉ። ለምሳሌ ብንወስድ የአክሱም ዘመነ መንግስት በዮዲት ጉዲት ከወደቀ ጊዜ አንስቶ እሰከ የዛግዌ ዳይናስቲ መመስረት ድረሰ እረዘም ያለ የግእዝ የስነፅሁፍ መቀዛቀዝ ታይቶ ነበር።

የአማርኛን የስነፅሁፍ በተመለከተ ደግሞ በአምስቱ አመታት የፋሽሽት ጣልያን ወረራ ወቅት ከተወሰኑ የፀረ የፋሽሽት የጋዜጣ ህትመት ዉጭ የፈጠራ ስራዎች ተkርጠ የነበረ ሲሆን በአብዮትና በለዉጥ ዘመንም ለምሳሌ 1965 እስከ 1972 አካባቢ የድርሰት ስራዎች የተዳከሙት ወቅትም ነበር።ብዙ ጊዜ የፈጠራ የስነፅሁፍ ስራዎች ሞቅ ብለዉ የሚሰሩት በተነፃፃሪ የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ ሲኖር መሆኑ ይታወቃል።

የፈጠራ የስነፅሁፍ ስራዎች (Creative writing) በብዛት የተደረሱባቸዉን ዘመናት ፖለቲካዊ ፣ ማህበረዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ያንፀባርቃሉ። በመሆኑም ልብ ወለዶችና ግጥሞች በአንድ ወቅት የነበረን የማህበረሰብ ስነልቦነዊ እና ማህበራዊ ለማጥናት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖራቸዋል። እናም የስነፅሁፍ ስራዎች የራሳቸዉን ዘመን ሁኔታ ስለሚያንፀባርቁ በዘርፉ ያሉ ምሁራን “የዘመኑ መንፈስ” መንፈሰ በሚል የየወቅቱን ፖለቲካዊ ፣ ማህበረዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ከጊዜ መቼት አንፃር ይተነትናሉ።

ለምሳሌ የአማርኛን የፈጠራ የስነፅሁፍን በተመለከተ የያዙቱን መንፈስ ለመመርመረ በየዘመናቱ ከፋፍሎ ማየት ይቻላል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የሃገራችንን የልብ ወለድ (Novel) የታሪክ ሂደት መመልከት ይቻላል።

 የኢትዮዽያ ስነፅሁፍ ታሪከ በአብዘኛዉ የግዕዝ ስነፅሁፍ ታሪክ ነዉ። በሀገሪቱ የግዕዝ ስነፅሁፍ ታሪክ የሶስት ሺህ ዘመናት ያህል ቆይታ ያለዉ ሲሆን የአማርኛ ቋንቋና ስነፅሁፍ ግን ከሁለት መቶ አመታት ያልበለጠ ታሪክ ያለዉ ነዉ። ምንም እንኳን የአማርኛ ቋንቋና የፈጠራ ስነፅሁፍ ቀደም ብሎ በእነ አፈወርቅ ግብረኢየሱስ “ጦቢያ” እና በነሂሩይ ወልደስላሴ “ወዳጄ ልቤ”፣ “አዲስ አለም” የተጀመረ ቢሆንም የልብ ወለድን መስፈርት ያሟላ የተባለለት ስራ የጀመረው ግን በደጃዝማች ተክለሀዋርያት 1941 ዓ∙ም∙ ላይ ነዉ።

 የአማርኛ እረጅም የልብ ወለድ (Novel) ታሪክ የሚጀምረዉ በ1941 ዓ∙ም∙ ከ “አርአያ” መታተም ጋር በተያያዘ ነዉ። “አርአያ” ለኢትዮዽያ ወይም ለአማርኛ ቋንቋ የመጀመሪያዉ የልብ ወለድ ታሪክ ሲሆን እረጅም ልብ ወለድም ለመባል ሁሉልም የልብ ወለድ አላባዉያልና እና የገፅ ብዛት በማሙላቱ ነዉ።

አርአያ በደጃዝማች ተክለሀዋርያት ከተፃፈበተ ማለትም ሀገሪቱ ከጣልያን ፋሽሽት ወረራ ነፃ ከወጣችበት እስከ “ታሀሣስ ግርግር” እስከሚባለዉ ጊዜ ያለዉ የመጀመሪያዉ የአማርኛ የልብ ወለድ ዘመን ሊባል የሚችል ሲሆን የዘመኑም ስራዎች የራሳቸዉ መነፈስ ያላቸዉ ነበሩ።

ከዚህ አነፃር ደጃዝማች ተክለሀዋርያት በዋናዉ ገፀባህሪ በአርአያ በዘመኑ የነበረዉን የወጣቶች የዉጭ የትምህርት እና ወደሀገረም ተመለሶ በሀገር ፍቅር ስሜት ማገልገለን የተመለከተ ሀሳቦች በጠቃላይም የሀገርን ፍቅር አጉለተዉ አሳይተዋል።

በዚያ ዘመን የነበሩ ሌሎች ደራስያንም በወቅቱ የነበረዉን የጣልያን ወረራ እና የአርነኞች ተጋድሎ፣ ሰለዘመናዊነትና ትምህርተ መስፋፋት በስራቸዉ አንፀባርቀዋል። በዚህ ወቀት የነበሩ አብዛኞቹ ጸሀፊዎች ከቤተክህነት የተገኙ ስለነበሩ በድርሰቶቻቸዉ ሃይማኖታዊ ስነምግባርን የሚያንፀባርቁ ነበሩ። ከዘመናዊ የረጅም ልብ ወለድ ቴክኒኮቸ አንፃር ብዙም አልነበሩም።

 የእረጅም የልብ ወለድ ሁለተኛ ዘመን ብለን የምንከፍለዉ ደግሞ ከታህሳስ ግርግር ማግስት እስከ አብዮቱ ፍንዳታ (1954­1966) ያለዉን ሲሆን በዚህ ወቅት ዘመናዊ ትምህርት የቀሰሙ ደራስያን ዘርፉን የተቀላቀሉበት ጊዜ ነበር። ፍቅር እስከ መቃብር ፣ ከአድማስ ባሻገር፣ አደፍርስ እና ሌሎችም የተደረሱበት ወቅት ነዉ። ስራዎቹም በወቀቱ ስለነበረዉ ማህበረሰብ ስለፊዉዳሊዝም የባህልና ትምህርት ሁኔታ አንጸባርቀዋል።

 ሌላኛዉ የልብ ወለድ ዘመን ከአበዮቱ ፍንዳታ እስከ 1975 ዓ∙ም∙ የሚመለከት ሲሆን በዘመኑም ከነባር ፀሀፊዎች የብርሃኑ ዘሪሁን እና የበአሉ ግርማ የአብዮት ወቅት ታሪኮች ጎልተዉ የሚታዩበት ነበር። በዚህ ዘመን የበአሉ ግርማ የቀይ ኮኮብ ጥሪ (1972) ፣ ደራሲዉ (1972) ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ሦስቱ ማዕበሎች / ማዕበል ­ የአብዮት ዋዜማ ፣ ማዕበል ­ የአብዮት መባቻ ፣ማዕበል ­ የአብዮት ማግስት/ ለህትመት የበቁበት ጊዜ ሲሆን እንደተለመደዉ በብዛት የወቀቱን መንፈስ ማለተም የአብዮቱን ዉጥንቅጦች አሳይተዋል።

 ከ1975 እሰከ 1983 ያለዉ በአማርኛ የፈጠራ ስራዎች እነደ አንድ አራሱን የቻለ ዘመን የመንቆጥረዉ ሲሆን በዚህ ወቅት ከነባሮቹ በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ ደራስያንን ያገኘንበት ወቀተ ነበር። ለምሳሌ ለመጥቀስም ሲሳይ ንጉሱ፣ ገበየሁ አየለ፣ ሀይለመለኮት መዋዕል ፣ አንዳርጌ መሰፍን ፣ የሺጥላ ኮኮብ እና ሌሎችም። ከድርሰትም አንፃር የሲሳይ ንጉሱን ሰመመንን፣ ግርዶሽን ፣ ትንሳኤን ያየንበት ሲሆን የገበየሁ አየለ ጣምራ ጦር ፣ ስደተኛዉ እና እንባና ሳቅ ታትመዋል። ሀይለመለኮት መዋዕልም የወዲያነሽንና ጉንጉንን አበርክቷ።

የዚህ ዘመን ድረሰቶችም በወቀቱ የነበረዉን የለዉጥ መንፈስ ፣ የተለያዩ የማህበራዊ ህይወት ሁኔታዎችን ፣ ከሶማሊያ ጋር ስለነበረዉ ጦርነት (የገበየሁ አየለ ጣምራ ጦር ) እና የመሳሰሉትን የዘመኑን መንፈስ የሚያሳዩትን መልእከቶች ይዳስሳሉ።

 ከ1983 በኋላ ደግሞ እነደነ ፍቅረ ማረቆስ ደስታ አይነቶች በጣም በርካታ አዳዲስ ደራሰያንና ስራዎች የፈለኩበት ዘመን ሲሆን በጭብጥ ደረጃም በወቀቱ የነበሩትን እነደ የአረብ ሀገራት ስደት ፣ ዲቪ ሎተሪ ፣ ኤች እይ ቪ ን ጨምሮ በጣም በርካታ ማህበራዊ መልክቶች የተላለፉበትና ትለቅ መነቃቃት የታየበት ዘመን ነበር ለማለት ይቻላል። ይሁንና ብዙዎች እንደሚሉት ይህ መጀመሪያ ላይ የነበረዉ የፈጠራ ስራዎች ድርሰትና ንባብ መነቃቃት በዚህ ወቅት ያለ አይመስልም።

እናም አሁን ያለነበት ዘመን ብዙዎች እነደሚሉት ከአማርኛ ልብ ወለድ ድርሰቶች ህትመት ብዛትና ንባብ እንፃር ብዙም የጠፋበት የጨለማ ዘመን ወይም ብዙ የተሰፋፋበት ወርቀማ ዘመን ባያስብልም የማህበረሰቡን ቁልፍ ቁልፍ ጉዳዮችን በጉልህ አዉጥቶ ከማሳየትና ከማነፀባረቅ አንፃር ደንገዝገዝ ያለበት ዘመን ይመስላል። በዚህ ዘመን ከልበ ወለድ እና የፈጠራ ስራዎች ይልቅ የፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳዮች ላየ ያጠነጠኑ መፃህፍት በብዛት የሚታተሙበትና የሚነበቡበት ጊዜ ነዉ። ይህም የዘመኑ የፈጠራ ስራዎች መነፈስን ለይቶ ይህ ነዉ ለማለት የሚያዳገተበት ወቅት ያደረገዋል።

ይሁንና አሁን ላይ ላሉን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችን መፍትሄ ለማበጅት ደራስያን አልመዉና አቅደው የበኩላቸዉን ሃሳብ በተጠናከረ መለኩ በፈጠራ ስራዎቻቸዉ ሊያቀርቡ ይገባል።

Related Post