አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ስለ ታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር

ስለ ታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር
ስለ ታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር

የገቢዎች ሚኒስቴር ለታክስ ህጎች ዓላማ ሲባል ታክስ ከፋዮችን ለመለየት የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር አዘጋጅቶ ይሰጣል፡፡

ለሁሉም የታክስ ህጎች አንድ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር የሚሰጥ ሲሆን አንድ ታክስ ከፋይ በማንኛውም ጊዜ አንድ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ብቻ ይኖረዋል፡፡

አጠቃቀም
1.የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር የተሰጠው ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን በማንኛውም የታክስ ማስታወቂያ ወይም ለታክስ ህግ ዓላማ ሲባል በሚቀርብ ወይም ጥቅም ላይ በሚውል ሰነድ ወይም በታክስ ህግ መሰረት በሚዘጋጅ ሰነድ ላይ መግለፅ ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም ታክስ ከፋዩ ታክስ ቀንሶ የማስቀረት ግዴታ ባለበት ሰው ክፍያዎች በሚፈፅምለት ጊዜ ታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን መስጠት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡

2.ማንኛውም የንግድ ስራ ለመስራት ፈቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ የሚያቀርብ ታክስ ከፋይ ፈቃድ ለሚሰጠው ባለስልጣን የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን መስጠት አለበት፡፡

3.ታክስ ከፋዩ ፈቃድ በሚያድስበት ጊዜ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ማቅረብ የሚጠበቅበት የመጀመሪያው የፈቃድ ማመልከቻ ከቀረበ ወዲህ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ የተቀየረ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

4.የንግድ ወይም የስራ ፈቃድ የሚሰጥ የመንግስት አካል ወይም ተቋም ታክስ ከፋዩ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን ሳያቀርብ ፈቃድ መስጠት አይችልም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ለተሰጠው ሰው ብቻ የሚያገለግል በመሆኑ ለሌላ ሰው ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም፡፡

5. የታክስ ወኪል የአንድን ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ሊጠቀምብት የሚችለው መቼ ነው ለሚለው ጥያቄ አንድም የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ ባለቤት የሆነው ሰው የታክስ ወኪል የታክስ መለያ ቁጥሩን ለመጠቀም እንዲችል በፅሁፍ ሲፈቅድለት አሊያም የታክስ ወኪሉ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩን ለታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ ባለቤት የታክስ ጉዳዮች ብቻ ሲጠቀምበት ነው፡፡

የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር መሰረዝ
የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ሚኒስቴሩ የሚከተሉት ምክንያቶች ሲያጋጥሙ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የአንድን ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር መሰረዝ ይችላል፡፡

1.የታክስ ከፋዩ እውነተኛ ማንነት ባልሆነ ማንነት የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥሩ የተሰጠ እንደሆነ
2.ታክስ ከፋዩ ጥቅም ላይ ያለ ሌላ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ያለው እንደሆነ ሚኒስቴሩ በማንኛውም ጊዜ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የአንድን ሰው የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) በመሰረዝ አዲስ የታክስ መለያ ቁጥር ሊሰጠው ይችላል፡፡
ምንጭ፡ የገቢዎች ሚኒስቴር

Related Post