ለታክስ ከፋይነት የመመዝገብ ግዴታ ያለባቸው ሰዎች አስቀድሞ የተመዘገበ ካልሆነ በስተቀር በታክስ ሕግ መሠረት ታክስ የመክፈል ኃላፊነት ያለበት ሰው በሚኒስቴሩ ዘንድ ለመመዝገብ ማመልከት አለበት፡፡
ተቀጣሪ አስቀድሞ የተመዘገበ ካልሆነ በስተቀር፣ ከቀጣሪው ጋር ውል የገባ ተቀጣሪ ይመዘገብ ዘንድ ቀጣሪው የማመልከት ግዴታ አለበት፡፡ ቀጣሪው እንዲመዘገብ ያላደረገው ተቀጣሪ ባይመዘገብ ካለበት የመመዝገብ ግዴታ ነጻ ሊያወጣው አይችልም፡፡ ለምዝገባው የሚቀርበው ማመልከቻ የሚከተሉትን በማካተት መቅረብ ይኖርበታል፡-
የጣት አሻራ መለያን ጨምሮ የግለሰቡን ማንነት ከሚያረጋግጥ የሰነድ ማስረጃ ጋር ተያይዞ መቅረብ አለበት፤
የታክስ ከፋዮች ለታክስ የመመዝገብ ግዴታ ካለበት ቀን አንስቶ በ21 (በሃያ አንድ) ቀናት ውስጥ ወይም ሚኒስቴሩ በፈቀደው ተጨማሪ ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት፡፡
አስቀድሞ የተመዘገበ ካልሆነ በስተቀር ታክስ የመክፈል ኃላፊነት ያለበት ሰው በባለስልጣኑ የመመዝገብ ግዴታ ያለበት ሲሆን ከተመዝጋቢዎች ውስጥ የሚከተሉት ይካተታሉ:-
በንግድ ወይም በሙያ ሥራ (መቀጠርን ሳይጨምር) የተሠማራ ግለሰብ፤
ቤት በማከራየት ገቢ የሚያገኝ ግለሰብ፤
ተቀጣሪ፤
የንግድ ማህበር፤
የመንግሥት የልማት ድርጅት፤
የመንግሥት ባለበጀት መ/ቤት፤
መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶች፤
የሃይማኖት ተቋማት፤
በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ኩባንያ በቋሚነት የሚሠራ ድርጅት፤
የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጪ መጋራት ተጠቃሚዎች፤
በጋራ ሀብትነት ያልተመዘገበ ሀብት ያላቸው ሰዎች፤
ባለ ልዩ መብት፤
በመንግሥታት መካከል በሚደረግ ስምምነት ወይም በጽ/ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት የሚቋቋሙ ድርጅቶች፤
የኩባንያ አክሲዮን ባለድርሻ፡፡
ለታክስ ከፋይነት መመዝገብ ያለበት ሰው እንደ ሁኔታው ሥራውን ከመጀመሩ ወይም ገቢ ከማግኘቱ በፊት ለታክስ ከፋይነት ለመመዝገብ የምዝገባ ማመልከቻ ማቅረብ አለበት፡፡
ምንጭ – የገቢዎች ሚኒስቴር