የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሸቱ 2፡30 ኮኬይን የተሰኘ አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር አዋሉ፡፡
ሦስት የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች መነሻቸውን ብራዝል-ሳኦፖሎ በማድረግ በኢትዮጵያ በኩል ወደተለያዩ ሀገራት 1,895 ጥቅል ፍሬ (42 ኪሎ ግራም) የሚመዝን ኮኬይን በቦርሳ ይዘው ለማለፍ ሲሞክሩ የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋላችውን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ አደጋኛ ዕፅ ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር አዲሱ ባለኒ ገልፀዋል፡፡
ኢንስፔክተሩ አያይዘውም ግለሰቦቹ በአየር መንገዱ ጣቢያ ውስጥ ግርግር በመፍጠር እና ከሰራተኞች ጋር በመጋጨት ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርጉም በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ መነሻዋን ብራዝል ሳኦፖሎ መዳረሻዋን ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ዱባይ ለማድረግ 1049 ጥቅል ፍሬ (21 ኪሎ ግራም ከ380 ግራም) የሚመዝን ኮኬይን ይዛ የተገኘች ብራዝላዊት የኢትዮጰያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋል መቻሏን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በዚህ 15 ቀን ውስጥ 2044 ጥቅል ፍሬ (63 ኪሎ ግራም ከ380 ግራም) ኮኬይን መያዙን ጠቁመዋል፡፡ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ተይዘው ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ሳያገኙ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር ከወጡ በኋላ በቀጠሮ ቀን ተመልሰዉ ሳይቀርቡ ስለሚቀሩ እና አደንዛዥ ዕፁን ይዘው ለሚገኙ ሰዎች የሚሰጥ ውሳኔ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ዝውውሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ የአዘዋዋሪዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ በመምጣቱ ህጉ መሻሻል አለበት ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዝውውሩን ለመከላከል በአየር መንገዱ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝና የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይም በወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተጣራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡