አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት ተጀመረ

የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት ተጀመረ
የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት ተጀመረ

የጉምሩክ ኮሚሽን የወረቀት አልባ የጉምሩክ አገልግሎት ስርዓት መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት በይፋ አስጀምሯል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ያሳለፍነው 2012 ዓ.ም በርካታ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን የተጠናቀቁበት ዓመት ነበር፡፡ 2013 ዓ.ም አዳዲስ ፕሮጀክቶች የሚጀመሩበት በሂደት ላይ ያሉት የሚጠናቀቁበት መሆኑን ጠቁመው የጉምሩክ ኮሚሽን ያስጀመረው የወረቀት አልባ አገልግሎት ከፕሮጀክቶቹ አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ባሳለፍነው በጀት ዓመት ዕቅዳቸውን ሙሉ በሙሉ (100 በመቶ) ካጠናቀቁ ጥቂት የመንግስት መስሪያ ቤቶች አንዱ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ይህ መልካም ጅምር የበለጠ አጠናክሮ ሰራተኞችን በስነምግባር የማነፁ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ተቋማትም ይህንን ፈለግ በመከተል አሰራራቸውን ዘመናዊና ቀላል ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ መሳካት አስተዋፅኦ ያበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአገልግሎቱ ማስጀመሪያ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው እንደገለፁት አዲሱ ስርዓት በተለይም አስመጪና ላኪዎች ደጋፊ ሰነዶችን ለማቅረብ የሚወስድባቸውን ጊዜና ወጪ ያስቀረ እንዲሁም ከወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አላስፈላጊ ንክኪና የአካል መቀራረብን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፡፡በዚህም መንግስት ከዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ ከፍ እንዲል ያደርጋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስራ ስነምግባርን በማስገኘት ፍትሃዊ አሰራርን እንደሚያረጋግጥ ገልፀዋል፡፡

ከአግልግሎት አሰጣጥ አንጻርም መንግስት ያስቀመጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያን መሠረት ያደረገ እና በተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጉምሩከ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው ኮሚሽኑ አሰራሩን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ተከታታይ የሆኑ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቶአል፡፡ የወረቀት አልባ የጉምሩከ አገልግሎትም የዚሁ አንድ አካል ነው ብለዋል

Related Post