አርእስተ ዜና
Fri. Nov 22nd, 2024

የኢትዮጵያ የ2015 በጀት በ17 በመቶ አደገ

የኢትዮጵያ የ2015 በጀት በ17 በመቶ አደገ
የኢትዮጵያ የ2015 በጀት በ17 በመቶ አደገ

ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ የ2015 በጀት በ17 በመቶ አደገ። የሀገሪቱን የ2015 ጥቅል በጀት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በመደልደል በድህነት ቅነሳ፣ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የተጎዱትን አካባቢዎች የትኩረት ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤ ትአመላክቷል፡፡

የተጀመሩ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ ተገቢውን በጀት ሊመደብላቸው እንደሚገባ ምክር ቤቱ አቅጣጫ ያመላከተ ሲሆን፤ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የሚመደብላቸውን በጀት ከብክነት በጸዳ እና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዳለባቸውም ከምክር ቤት አባላት ሀሳብ ተሰጥቷል፡፡

የሀገር ሠላምና ደህንነት የሚረጋገጠው ዜጎች በልተው ሲያድሩ እና ለወጣቶች የስራ ዕድል ሲፈጠርላቸው እንደሆነ የገለጹት የምክር ቤት አባላት፤ በቀጣይ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እና የድህነት ቅነሳን አስመልክቶ የ2015 ጥቅል በጀት አበረክቶው ምን ሊሆን ይችላል? ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ሀገራዊ የቤት እና የሕዝብ ቆጠራ ባልተካሄደበት ሁኔታ እንዴት የበጀት ድልድሉ ፍትሐዊ ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄም ከምክር ቤቱ ተነስቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አህመድ ሺዴ ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየት አዘል ሀሳቦች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ የ2015 በጀት ድልድሉ ፍትሐዊ እና ድህነት ቅነሳን ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ክልሎች እና በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በጀት ዓመት 20 ቢሊየን ብር በጀት እንደሚያዝ ነው የገለጹት፡፡

በጦርነቱም ሆነ በድርቁ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ፤ ከዓለም ባንክ የ300 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት መደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል ድልድሉ ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመገንባት እና የዜጎችን ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሲባል በበጀት ድልድሉ ለሀገር መከላከያ ሥራዊት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ክቡር ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በ2015 የፌዴራል መንግሥት ጠቅላላ ገቢ የውጭ እርዳታን ጨምሮ 477 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር እንደሚሆን የታቀደ ሲሆን፤ ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገንዘብ 92 በመቶ እንደሚሸፍን ያስረዱት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፤ አጠቃላይ የሀገሪቱ የወጪ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም፤ ሀገሪቱ ከውስጥም ከውጭም በደረሰባት ጫና በኢኮኖሚው አሉታዊ ተፅዕኖ ቢደርስም፤ በልማት ፕሮጀክቶች እና በግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ የተሻለ ውጤት የተመዘገበ መሆኑን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

አርሶ-አደሩ የማዳበሪያ እጥረት እንዳይገጥመው ቀደም ብሎ ግዥ ተፈፅሞ ወደ ሀገር እየገባ ሲሆን ፍትሐዊ ስርጭት እንዲኖር አስፈላጊው ቁጥጥር እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የገንዘብ ሚኒስቴር ባቀረበው የ2015 ረቂቅ በጀት ከተወያየ በኋላ፤ ረቂቅ አዋጅ 8/2014 በማድረግ ለምክር ቤቱ ፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቶታል፡፡

Related Post