አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የችሎት ክትትል አጭር ሪፖርት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የችሎት ክትትል አጭር ሪፖርት

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጃዋር ሲራጅ መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በ23 ግለሰቦችና በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ድርጅት ላይ የመሰረተው ክስ ዛሬ መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተነቧል።

ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር በችሎት የተገኙ ሲሆን 11ኛ፣ 14ኛ እና 15ኛ ተከሳሽ የሆኑት ደጀኔ ጉተማ፣ ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ እና ጸጋዬ ረጋሣ አራርሳ በሌሉበት ተከሰዋል። ተከሳሾቹ በተለያየ አይነት ድርጊቶች ተጠርጥረው የተከሰሱ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩት ተከሳሾች ላይ የቀረበው ክሶች፡-

● የወንጀል ሕጉን አንቀፅ 32/1/ሀ እና ለ፣ አንቀፅ 35፣ አንቀፅ 38 እና አንቀፅ 240 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የመገናኛ ብዙሀን እንዲሁም ማህበራዊ የትስስር ድረ-ገፆችን በመጠቀም አንዱን ብሔር በሌላው ብሔር ላይ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲያነሳ እንዲሁም ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲነሳ በማድረግና በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ በመሆን፣

● የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀፅ 6/2/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም በማቀድ እና በመሰናዳት፣

● የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ ቁጥር 761/2004 አንቀፅ 9/1/ሀ/ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ያለ ሕጋዊ ፈቃድ የተከለከሉ የቴሌኮም መሳሪያዎች በመያዝና የቴሌኮም መሰረተ ልማት በመዘርጋት እና

● የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 የተመለከተውን በመተላለፍ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖር የጦር መሳሪያ በመያዝ ወይም በማስቀመጥ የሚሉ ናቸው።

እንዲሁም ዐቃቤ ሕግ እንደክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን 146 የሰው ምስክሮችን እንዲሁም 20 የሰነድ፣ 2 ገላጭ እና 10 የኤግዚቢት ማስረጃዎችን ዝርዝር የገለጸ ሲሆን 146ቱ የሰው ምስክሮች በወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 መሰረት ጥበቃ የሚደረግላቸው መሆናቸውንም አመልክቷል።

ደጀኔ ጉተማ፣ ብርሃነመስቀል አበበ እና ጸጋዬ አራርሳን በተመለከተ ፖሊስ ከሃገር ውጪ መሆናቸውን በመግለጹ በጋዜጣ ማስታወቂያ ጥሪ እንዲደረግላችቸው ፍ/ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል። የዋስትና ጉዳይን በተመለከተ ሁሉም ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በ15 ዓመት ወይም ከዛ በላይ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑና በድርጊቱም የሰው ሕይወት ጠፍቷል በመባሉ በወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ መሰረት የዋስትና መብት አይፈቀድም በማለት ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ሆነው ክሱን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾች በክሱ ላይ የሚያቀርቡት መቃወሚያ ካለ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሬጅስትራር ጽ/ቤት እንዲያስገቡና የዐቃቤ ሕግን መልስ ለመስማት ለህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል።

Related Post