አርእስተ ዜና
Fri. Nov 22nd, 2024

የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የአቋም መግለጫ አወጣ

የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የአቋም መግለጫ አወጣ
የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የአቋም መግለጫ አወጣ

ከየካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ሲከናወን የቆየው የመጀመርያው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ የሚከተሉትን ባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አወጣ።

1ኛ. የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በማስፋት እና በማጽናት የህዝባችንን ሁለንተናዊ ደህንነት ማረጋገጥ የፓርቲያችን ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ የውስጠ ፓርቲ ጤንነታችንን መጠበቅ ከሌብነትና ከተደራጀ ስርቆት አንጻራዊ ነጻነቱን የጠበቀ የአመራር ስምሪት ማረጋገጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ የአገልጋይ አመራር ስብዕናን የተላበሰ ጠንካራ የፓርቲ መስተጋብር ለመፍጠር ወስነናል፡፡

ያለጠንካራ ፓርቲ ግንባታ እቅዶቻችንን ማሳካትም ሆነ የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለማንችል ለዚህ ዘርፍ የተለየ ትኩረት የምንሰጥ መሆኑን እናረጋግጣለን፤ ለዚህም ቃል እንገባለን፡፡

2ኛ. የየአገራችንን አንድነት እና የህዝባችንን ሰላም በጽኑ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ መድረኩ የሚጠይቀንን እና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ተዘጋጅተናል፡፡ ስለሆነም ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ለአገራዊ አንድነት ተጠናክሮ መውጣት፣ለዜጎች ክብር እና ነጻነት እንዲሁም በህይወት የመኖር መብት መረጋገጥ እና የአካል እና የንብረት ደህንነት መከበር በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መስራት እንዳለብን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡

ስለሆነም አገራዊ መግባባት ማምጣት የሚያስችል አካታች ብሄራዊ ምክክር በማድረግ በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን ማጥበብ የሚያስችል ፈጣንና መላውን ህዝብ ያሳተፈ ምክክር በማድረግ በህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ ዘላቂ እና የማያዳግም እምርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ስለሆነም በተባበረ ጥረት ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን በመገንባት፣በህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝም መሰረት ላይ የታነጸ አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ቃል እንገባለን፡፡

3. በተጨባጭ ውጤት የሚገለጽ የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ እውን እንዲሆን በጋራ መረባረብ አለብን፡፡የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም የበለጸገ አስተሳሰብ ውጤት እንጂ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ሰለባ መሆን የለበትም፡፡ እርስ በእርስ አለመከባበር፣ መዘላለፍ፣ በአደባባይ ላይ ሳይቀር ጸያፍ ድርጊት መፈጸም፣ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና ለእህትማማችነት የማይመጥን ጸረ አንድነት የሆነ ከፋፋይ ድርጊት መፈጸም የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ጸር እንደሆነ ጉባኤያችን ያምናል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝሀነት አገር መሆኗ ግልጽ ሆኖ እያለ ከእኛ ይልቅ እኔብቻ በሚል ተነጣይ አስተሳሰብ መጠመድ፣ ሽማግሌዎችን እና የማህረሰቡን ጉልሀን መዝለፍ፣ የቡድን መብትን አለማክበር፣ ብዝሀነትን ማጣጣል፣ የመንግስት ሹመኞችን ከግብረገብነት ባፈነገጠ መልኩ ማንቋሸሽ ኢትዮጵያዊ ልማድ ካለመሆኑም በላይ ዴሞክራሲን የሚያቀጭጭ ኋላ ቀር ድርጊት በመሆኑ ድርጊቱን የሆነ ቦታ መግታት ካልቻልን አገራችንን ብዙ አመት ወደኋላ የሚጎትት እና በውጥን የሚያስቀረን የብልጽግና ጉዟችን እንቅፋት ነው፡፡

እርስ በእርስ በመቻቻል እና በመከባበር፣ ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር እምርታዊ ለውጥ በማምጣት አገራችንን ወደፊት ሊያስፈነጥር የሚችል የተግባቦት ስራ መስራት ይኖርብናል፡፡የፍትህ አካላት ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የሚኖራቸውን አበርክቶ አስፍተውና አልምተው መተግበር አለባቸው፡፡ ለዚህም በጋራ መታገል ይኖርብናል፡፡ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የሚሳካ አይደለም፡፡

ሌብነትን የማይሸከም አሰራር እና ፖለቲካዊ ከባቢ መገንባት የሁላችንም ግዴታ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ስለሆነም ከመላው ህዝባችን ጋር በመተባበር እና በመቀናጀት አገር በቀል እሴቶቻችንን በመጠበቅና በመንከባከብ፣ እርስ በእርስ በመከባበርና በመቻቻል በጅምር ላይ የሚገኘውን የአገራችንን ዴሞክራሲ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ቃል እንገባለን፡፡

4ኛ. ኢኮኖሚያዊ መልሶ ማቋቋምና የአስር አመት ዕቅድ ትግበራ ስራችን ላይ ፈርጀ ብዙ ስራ በመስራት የአገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ የህዝባችንን የነፍስ ወከፍ ገቢ እንዲጨምር ማድረግ በአጠቃላይ የህዝባችንን ኑሮ አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ ማሻሻል አለብን፡፡

አፋጣኝ መፍትሄ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ፈጣን እርምጃ መውሰድ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ ምንም እንኳን የአለም አቀፍ ሁኔታው ለገበያ ጉድለት መፈጠር የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረውም ወቅታዊ የሆነውን የህዝባችንን የኑሮ ውድነት ችግር ለማሻሻል ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለብን እናምናለን፡፡
የመሰረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦት ችግር፣ የኑሮ ውድነት፣ በገቢና በወጭ ምርት ላይ የሚታይ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የስራ አጥነት ችግር በዘላቂነት የሚፈታበትን ትልም ከወዲሁ ቀይሶ የህዝባችንን ሸክም ማቃለል እንዳለብን በጉባኤው ተመላክቷል፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ የብዝሀ ልማት ዘርፍን ማጠናከር፣ በግብርና ልማት ዘርፍ እምርታዊ ለውጥ ማምጣት፣ ቢያንስ ከውጭ ወደውስጥ የስንዴ ምርትን የማያስገባ የግብርና አቅም መገንባት፣ የማዕድን ሀብታችንን አሁን ካለበት ወደፊት እንዲስፈነጠር ማድረግ፣ የኢንዱስትሪንና የቱሪዝምን እድገት ሊያረጋግጡ የሚችሉ አማራጮችንና ዘዴዎችን መከተል እንዳለብን ጉባኤያችን አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤ እስከሚቀጥለው ጉባኤ ድረስ መሳካት አለባቸው ብሎ ባስቀመጣቸው የልማት አጀንዳዎች ላይ ቀን ከሌት ተረባርቦ ተስፋ ሰጭ ውጤት ማስመዝገብ እንዳለበት መተማመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለተግባር ስኬታችንም ቃል እንገባለን፡፡

5ኛ. የአገራችንን ሉአላዊነት እንደወትሮው ሁሉ ለማረጋገጥ ዝግጁ ነን፡፡ ምንም እንኳን ከውስጥም ከውጭም የሚፈታተኑን ኃይሎች በርካታ ቢሆኑም ማንኛውንም ጥቃት መቋቋም የሚችል የውስጥ አቅም ለመፍጠር እየተረባረብን እንገኛለን፡፡

በተለይም ጦርነትንና ግጭትን የሚያስቀር ጠንካራ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንዳለብን ጉባኤያችን በአንክሮ ተመልክቶታል፡፡
የታላቁን ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ አንድ አገራዊ ወሳኝ ተልዕኳችን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ብዥታዎችን ያለማመንታት መቅረፍ እንዳለብን እናምናለን፡፡ ለጎረቤት አገሮች የምንሰጠውን ልዩ ትኩረት አጠናክረን በመቀጠል የቀጠናውን ትብብር ማሻሻል እና የኢትዮ ኤርትራን ግንኙነት የበለጠ ማጽናት አለብን ብለን እናምናለን፡፡

ድህረ ጦርነት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የመላውን ህዝባችንን ማህበራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ሳንታክት እንሰራለን፡፡ ዜጎች በርሀብና በድርቅ እንዳይጎዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ኢትዮጵያዊ ወንድማማችንትንና እህትማማችነትን ማጎልበት፣ እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላችንን ከፍ ማድረግ፣ አንዳችን ለሌላችን ያለንን ፈጥኖ ደራሽነት ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡

ስለሆነም በጦርነትና በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በቅድመ ጥናት እና በጥንቃቄ ላይ ተመስርተን ወደየቀያቸው የሚመለሱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለህዝባችን ሰላማዊ አኗኗር ስረ ምክንያት የሆኑ የሽብር፣ የጽንፈኝነት እና የማን አለብኝነት ዝንባሌዎችን በእንጭጩ እየቀጨን የህዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል እንዳለብን እናምናለን፡፡

በሁሉም አካባቢ የወደሙና የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት አለም አቀፍ ጫናን ተቋቁሞ ሉአላዊነትን የሚያጸና ዲፕሎማሲያዊ አቅጣጫዎችን ለመከተል አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ አለብን፡፡

6ኛ. የሀገራችን ፖለቲካ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ባለው ፋይዳ ልክ መቃኘት አለበት፡፡ አገራዊ አንድነትን የሚያጸና፣ አብሮነትን የሚያጎለብት፣አገር በቀል እሴቶቻችንን ለላቀ ጥቅም የሚያውል፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችንን የሚያቀል እንዲሆን መስራት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አኳያ ጠንካራ የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ስራ መስራት አለብን፡፡

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታችንን በማጠናከር የአንደኛውን ህመም ሌላኛው የሚጋራበት፣ በሌላኛው ጫማ ላይ ቁሞ ቁስልን የሚረዳበት እርስ በእርስ የመተጋገዝ፣ የመከባበር እና የመቻቻል ዘመናዊ የፖለቲካ ባህል መገንባት አለብን ብለንም እናምናለን፡፡

ዴሞክራሲን እየናፈቅን ዴሞክራሲ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል የማንፈቅድ ከሆንን ዴሞክራሲ በዘፈቀደ አይገኝም፡፡
ብልጽግናን እና የህዝባችንን ኑሮ መሻሻል እየተመኘን ነገር ግን ሁሉ ነገራችን ፖለቲካ ብቻ ከሆነ ያሰብነው አይሳካም፡፡
ሰላምና ጸጥታን እየፈለግን ነገር ግን በየመንገዱ ለጸብ፣ ለክርክርና ለጥላቻ መሰረት የሚሆን ስድብ፣ ዘለፋ፣ ስም ማጥፋት እና አብሪተኝነትን የምናስቀምጥ ከሆነ ሰላም በምኞት ብቻ ሊሳካ አይችልም፡፡ ስለሆነም በማህበራዊ ድረገጽ ትስስርም ሆነ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ዘወትር የምንናፍቀው የህዝባችን ሰላም እና የአገራችን አንድነት እንዲሳካ መረባረብ አለብን፡፡
በመጨረሻም የብልጽግና ፓርቲ የመጀመርያው ጉባኤያችን በመከረባቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ አጽንኦት ሰጥቶ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን ለህዝባችን ሁለንተናዊ ሰላም ደህንነት እና ተጠቃሚነት መረጋገጥ በፍጹም ቁርጠኝነት የምንሰራ መሆኑን እያረጋገጥን ጉባኤያችን በታላቅ ስኬት የተጠናቀቀ መሆኑን ለመላው ህዝባችን እናበስራለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለብልጽግና ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣ ለሁሉም የእምነት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ለአገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፣ ለምሁራን እና ለንግዱ ዘርፍ የማህበረሰብ አባላት፣ ለባለሀብቶች፣ ለወጣቶች እና ለሴቶች፣ አገራችሁን በተለያዩ መስኮች ለምታገለግሉ ውድ ኢትዮጵያውያን፣ ለአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት እና በፌዴራል፣ በአዲስ አበባ ፣ በድሬዳዋና በሁሉም ክልሎች የምትገኙ የፀጥታ አባላት፣ በውጭ አገር ለምትገኙ የዲያስፖራ አባላት ፣ በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ አገር የሚጸናው፣ የሚያድገው እና የሚበለጽገው በሁሉም ዜጋ የጋራ እርብርብ ነው በሎ ፓርቲያችን ብልጽግና ያምናል፡፡ ስለሆነም እናንተን ሳንይዝ የምናሳካው አንዳችም ነገር ስለሌለ በሁሉም መስክ የተለመደውን አገራዊ ግዴታችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እያስተላለፍን ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር፣ ለህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት በጋራ እንድንቆም የአደራ መልዕክታችንን ስናስተላለፍ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡
ብዝሃነት ጌጣችን ኢትዮጵያዊነት መገለጫችን ነው !!!
መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Related Post