በእትዮፕስያ በአሁኑ ወቅት በ400 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑ አንድ የግብርና ሚኒስቴር ሃላፊ ገለጹ።
ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሃገር ውስጥ ለመተካት እየተደረገ ባለው ሰፊ ርብርብ አበረታች የሆነ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል በማለት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ገርማሜ ጋሩማ ተናግረዋል። እንደ ሀገር በዘንድሮው የምርት ዘመን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 400 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 16 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ በመግባት እስከ አሁን ባለው የምርት አሰባሰብ መረጃ መሰረትም በአማካኝ ከ1 ሄክታር ከ30-60 ኩንታል ምርት እየተገኘ ሲሆን የታቀደውንም እቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት የሚያስችል ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትልቅ ትኩረት በመስጠት የባለሙያ ድጋፍ፣ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ከሎጅስቲክስ አኳያ የመስኖ ስንዴ ልማት በሚለማባቸው አካባቢዎች ላይ ስራውን በተቀናጀ ሁኔታ መስራት እንዲያስችል የተሽከርካሪ ድጋፍ አድርጓል ሲሉ ዳይሬክተር ጀኔራሉ ገልፀዋል፡፡
በሁሉም አካባቢዎች ምርት እንዳይባክን በሰፋፊ ኩታ-ገጠም እርሻዎች ላይ በሜካናይዜሽን የታገዘ የምርት አሰባሰብ ስራ እየተሰራ ሲሆን በተጨማሪም የገበያ ትስስር ችግር እንዳይፈጠርም ከክልሎችና ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር በመሆን የተመረተውን ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል ሲሉ ዳይሬክተር ጀኔራሉ አክለውም ገልፀዋል፡፡
በዘንድሮው አመት በመስኖ ስንዴ ልማት ያልተሳተፉ አርሶና አርብቶ አደሮችን በቀጣይ አመት ወደ ስራ እንዲገቡ የተለያዩ የልምድ ልውውጥና የመስክ ጉብኝት ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው ልምድ በመቅሰም ወደ መስኖ ስንዴ ልማት እንዲገቡ የሚያስችል ስራ የተሰራ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት የምርት ዘመንም 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴን ለማልማት እቅድ መያዙን አቶ ገርማሜ ጋሩማ ገልፀዋል፡፡
(ምንጭ – የግብርና ሚኒስቴር)