አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የሲሚንቶ ስርጭትና ዝዉዉርን ለመወሰን የወጣዉ የህዝብ ማስታወቂያ ተነስቷል

የሲሚንቶ ስርጭትና ዝዉዉርን ለመወሰን የወጣዉ የህዝብ ማስታወቂያ ተነስቷል
የሲሚንቶ ስርጭትና ዝዉዉርን ለመወሰን የወጣዉ የህዝብ ማስታወቂያ ተነስቷል

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ህገ-ወጥ ግብይትና ዝውውርን ለመከላከልና ለማስቀረት በቁጥር 001/2014 በቀን 06/01/2015 ዓ.ም በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ወጥቶ የነበረዉ የሲሚንቶ ስርጭትና ዝውውር መወሰኛ የህዝብ ማስተወቂያ ከታህሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተነሳ መሆኑን አስተውቋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያደገ በመጣዉ የግንባታ ዘርፍ እና ሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች በሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል በተፈጠረዉ አለመጣጣምን ተከትሎ ተከስቶ የነበረዉን ህገ-ወጥ የሲሚንቶ ምርት ግብይት በማስተካከል ከፍተኛ ህዝባዊ ጠቀሜታ ያላቸዉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት በቀጥታ ከፋብሪካ እንዲስተናገዱና ቀሪው ለግል አልሚዎችና ሲሚንቶን በግብዓትነት ለሚጠቀሙ አካላት በተተመነ ዋጋ ባጠረ ሰንሰለት ከአቅራቢዎች እንዲያገኙ ለማድረግ የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያ በማውጣት ሲሰራ እንደነበር ተብራርቷል፡፡

የወጣውን መመሪያ መሰረት በማድረግ ከመመሪያው ውጭ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ግብይትና ዝውውርን ለማስቀረት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ የህዝብ ማስታወቂያ በቁጥር 001/2014 በቀን 06/01/2015 ዓ.ም ወጥቶ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የሲሚንቶ ግብይትና ዝዉዉር መወሰኛ የህዝብ ማስታወቅያ ከታሕሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንዲነሳ የተወሰነ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለክቡራን ደንበኞቹ ያሳውቃል፡፡

በተያያዘ ዜና የሲሚንቶ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከገንዘብ ትርፍ የዘለለ ማህበረሰብን የማገልግል ሞራልን ይዘው ሊሰሩ ይገባል ተባለ። የሲሚንቶ አቅርቦትና ፍላጎት ባለመመጣጠኑ ምክንያት ለሀገራዊ እድገት በሚኖራቸው ፋይዳ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ቅድሚያ በመስጠት ያለውን ውስን የሲሚንቶ ምርት ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለማዳረስ ሲባል የሲሚንቶ አቅርቦትና ሥርጭቱ በመንግስት ብቻ ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ይህም አሰራር ከታህሳስ 14/2015 ዓ.ም ጀምሮ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን የተደረገውን የአሰራር ለውጥ ተከትሎ የሲሚንቶ አምራቾች ማህበር በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በተደረገው ማሻሻያም የሲሚንቶ አቅርቦትና ሥርጭት ሂደትን ለመቆጣጠር ትልቁን ኃላፊነት የተሰጠው ለአምራቾች ነው፡፡ መንግስት ሲሚንቶ በፋብሪካዎች በር የሚሸበትን ዋጋ የተመነ ሲሆን ይህንን መነሻ በማድረግም አከፋፋችና ቸርቻሪዎች ገንዘብ ከማትረፍ በዘለለ ማህበረሰብን የማገልገል ማህበራዊ የሞራል ግዴታ ስላለባቸው አሰራሩን አክብረው መስራት እንዳለባቸው ማህበሩ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

ንግድ ማለት ገንዘብ ማትረፍ ብቻ ባለመሆኑ ለማህበረሰባችንና ለደንበኞቻችን ስል በተፈቀደልን ዋጋ እና አሰራር ብቻ መሸጥ አለብን ሲልም ማህበሩ አክሏል፡፡
በአዲሱ አሰራር መሰረት የሲሚንቶ አምራቾች የሚመርጧቸው አከፋፋዮች ቸርቻሪዎቻቸውን መርጠው ለፋብሪካዎች ማሳወቅ ያለባቸው ሲሆን ከተመረጡት ውጪ ማንኛውም ሰው ሲሚንቶ መሸጥ አይችልም፡፡

በአሰራሩ ተካተው ሲሚንቶ የሚሸጡ ቸርቻሪዎችም የሚሸጡበትን ዋጋ የመለጠፍ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን ዋጋ የማይለጥፉና ከአሰራሩ ውጭ የሚንቀሳቀሱትን ማህበሩ ከፋብሪካዎችና ከመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ክትትል እንደሚያደርግም የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ሀይሌ አሰግዴ ገልጸዋል፡፡

መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ጨምሮ እየተገነቡ ያሉ ተጨማሪ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተጠናቀው ወደ ማምረት ስራ ሲገቡ አሁን ያለው የሲሚንቶ አቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ሙሉበሙሉ እንደሚቀረፍም አቶ ሀይሌ ጠቁመዋል፡፡

Related Post