አርእስተ ዜና
Wed. Nov 13th, 2024

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 120 ሚሊዮን ብር አተረፉ

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 120 ሚሊዮን ብር አተረፉ
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 120 ሚሊዮን ብር አተረፉ

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ስር የሚገኙ በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ አምስት የልማት ድርጅቶች በ2013 በጀት የመጀመሪያው አጋማሽ ዓመት ብር 119.9 ሚሊዮን አተረፉ፡፡

የልማት ድርጅቶቹ ይህንን ትርፍ ሊያገኙ የቻሉት በበጀት ዓመቱ አጋማሽ የንግድ፣ የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት በመስጠት በድምሩ ብር 4.56 ቢሊዮን ሽያጭ ገቢ ለማግኘት አቅደው ብር 2.76 ቢሊዮን ወይም የዕቅዳቸውን 60.5 በመቶ ገቢ በማግኘታቸው እንደሆነ በግምገማው ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ተገለጸው የድርጅቶቹ የዕቅድ አፈጻጸም የኤጀንሲውና የልማት ድርጅቶቹ ቦርድ እና ማኔጅምነት አባላት በተገኙበት ከየካቲት 1 እና 2 ቀን 2013 ዓ.ም በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሔደ ስብሰባ በተገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት የልማት ድርጅቶች የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣ ፍል ውሃ አገልግሎት ድርጅት፣ግዮን ሆቴል ድርጅት እና የልማትና ሆቴል ማህበር አ.ማ(ሂልተን ሆቴል) ሲሆኑ፣ ከእነዚህ የልማት ድርጅቶች አራቱ የውጭ ሽያጭ የሚያከናውኑ በመሆኑ በአጋማሽ ዓመቱ 16.36 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅደው 9.09 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማግኘት የዕቅዳቸውን 55.6 በመቶ አከናውነዋል፡፡

ግምገማውን የመሩት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል ሲሆኑ፣በግምገማው የድርጅቶቹ የኦፕሬሽን ፣የፋይናንስ ፣የፕሮጀክት፣ የሪፎርም እና የኮርፖሬት አስተዳደር ሥራዎች ግብ አፈፃፀም እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች አጽንኦት ተደርጎባቸዋል፡፡

በኦፕሬሽን አፈጻጸም በተለይም በሽያጭ ገቢ ብር 2.3 ቢሊዮን በማግኘት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የኢትዮጵ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሲሆን፣የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ደግሞ ብር 252.9 ሚሊዮን ገቢ በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ አብላጫ ድርሻ ይዟል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንጻር የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የአሜሪካ ዶላር 5.67 ሚሊዮን በማግኘት ግንባር ቀደም ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ የአሜሪካን ዶላር 2.89 ሚሊዮን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ ግዮን ሆቴሎች ድርጅትና ሂልተን ሆቴልም መጠነኛ የውጭ ምንዛሪ አግኝተዋል፡፡

በንግድ፣ ቱሪዝምና ሆቴል አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ኮቪድ-19 ባስከተለው ተጽዕኖ የተነሳ ብዙዎቹ ለኪሳራ በተዳረጉበት ወቅት በኤጀንሲው ሥር ያሉት ድርጅቶች አፈጻጸም የተሻለ ሆኖ መገኘቱ አበረታች መሆኑ በግምገማው ወቅት ተገልጾ፣ በቀጣዩ መንፈቅ ዓመት ጠንክረው በመሥራት የዓመቱን ግብ እንዲያሳኩ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቅጣጫ ሰጥተው የዕለቱ ግምገማ ተጠናቋል፡፡

Related Post