አርእስተ ዜና
Wed. Nov 13th, 2024

የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግሥት ባለሙያዎችን አስተያየት ሊቀበል ነው

የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግሥት ባለሙያዎችን አስተያየት ሊቀበል ነው
የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገመንግሥት ባለሙያዎችን አስተያየት ሊቀበል ነው

በኢትዮጵያ ከተከሰተው የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ሕገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሊራዘም በሚችልበት ሁኔታ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እልባት ለመስጠት እንዲረዳው ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው በግልጽ በተጠቀሱ ሶስት አንቀጾች ላይ የውሳኔ ሐሳብ እንዲሰጥባቸው ለሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መመራታቸውን ተከትሎ ጉባኤው ለውሳኔ እንዲረዳው ከፍተኛ የሕገመንግሥት ባለሙያዎች አስተያየት እንዲያቀርቡ ጋበዘ፡፡

የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስብሰባ አዳራሽ ይህን የገለጹት ጉዳዩን አስመልክቶ ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን ለጉባኤው የመራው ሚያዚያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም መሆኑን የገለጹት ክብርት ሰብሳቢዋ የጉዳዩን ክብደት ከግንዛቤ በማስገባት እስካሁን ድረስ የጉባኤው አባላት ባካሔዱት ስብሰባ ጉባኤው ጉዳዩን ለማየት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት ሕጋዊ ሥልጣን ያለው መሆኑን በማረጋገጥ ለሥራው ዕቅድ አውጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት መጀመሪያ ስለሕገመንግሥት አተረጓጎም ሒደትና በአገራችን ስለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቦርዱ አባላት ግምገማ (Assessment) እንደሚደረግና ይህን ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ጥያቄና በዚህ ላይ ጉባኤው በያዘው ጭብጥ ዙሪያ ከፍተኛ የሕገመንግሥት ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መድረክ እንደሚዘጋጅ ገልፀዋል፡፡

በሚዘጋጀው መድረክ ላይ በተጋባዥ ከፍተኛ የሕገመንግሥት ባለሙያዎቹ ጉዳዩን የተመለከተ አስተያየት (Amicus brief) በጽሑፍ እንደሚቀርብ እንዲሁም ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ እንደሚዘጋጅና ሒደቱም ወደፍርድ ቤት አሠራር የቀረበ እንደሚሆን ክብርት ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የሚሳተፉት ከፍተኛ የሕገመንግሥት ባለሙያዎች ተለይተው አስተያየታቸውን በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ቅዳሜ ግንቦት 8/2012 ዓ.ም እና ሰኞ ግንቦት 10/2012 ዓ.ም ለሕዝብ ይፋ በሚሆን መንገድ የሚያቀርቡ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የጉባኤው አባላት ከባለሙያዎቹ የሚቀርቡ አስተያየቶችን በማዳመጥ እና በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጽሑፎችን በማየት እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ግልጽ ውይይትና ክርክር በማድረግ ትርጉም እንዲሰጥባቸው የቀረቡት የሕገመንግሥቱ አንቀጾች ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ወይም አያስፈልጋቸውም በሚለው ጉዳይ ላይ ዝርዝር የውሳኔ ሐሳብ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 82(2) መሠረት የህገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ 11 አባላት የሚኖሩት ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት እና ም/ፕሬዚዳንት የጉባኤው ሰብሳቢና ም/ሰብሳቢ እንደሚሆኑም ይደነግጋል፡፡

Related Post