አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

ከ28 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

ከ28 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ
ከ28 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

በስድስት ቀናት ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና የንግድ ማጨበርበሮች ተያዙ፡፡

ዋጋቸው 28.2 ሚሊዮን ብር የሚገመት ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እና የንግድ ማጭበርበሮች ከነሐሴ 15-20/2012 ዓ.ም ባሉት ቀናት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 4 ሚሊዮን ብር የኢትዮጵያ ብር በህገ-ወጥ መንገድ ከሶማሌላንድ ወደ ጅግጅጋ በጭነት መኪና ሲጓጓዝ የተያዘ ሲሆን ሊሰወር የነበረ 15.78 ሚሊዮን ብር ቀረጥና ታክስ በኮምቦልቻ፣ በሞጆ እና በቃሊቲ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ክትትል ተደርሶባቸው ለመንግስት ገቢ ተደርጓል፡፡ ሌሎች በቁጥጥር ከዋሉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ የተለያዩ አልባሳት እና የግንባታ ዕቃዎች ይገኙበታል፡፡

3.04 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው የውጭ ምርት የሆነ ማሽላ የእርዳታ እህል በማስመሰል የጉምሩክ ስነስርዓት ሳይፈጸምበት ወደ መሐል ሲጓጓዝ እንዲሁም 2.7 ሚሊዮን ብር የሚገመት በቱሪስት ስም ገብቶ የጉምሩክ ህግን በመተላለፉ በድሬዳዋ የጉምሩክ ቅርንጫፍ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ሌሎች ግምታዊ ዋጋ ያልወጣላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎችም በተጠቀሰው ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ህጋዊ ንግድን ሽፋን በማድረግ የሚፈፀሙ የንግድ ማጭበርበሮች ለመከላከል በኮምቦልቻ፣ በሞጆ እና ቃሊቲ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች በመሆናቸው በሌሎችም ቅርንጫፎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ከሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት የሚሰጣቸውን ማበረታቻዎች ከታመለት ዓላማ ውጪ የሚጠቀሙት ላይ በተለይም በተደጋጋሚ የምንሰማው በቱሪስት ስም በማስገባት ከቀረጥና ታክስ ለመሸሽ የሚደረገው ሙከራ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል የሚያስፈልገው በመሆኑ ይህንን የምታስፈጽሙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የተጀመረውን ኮንትሮባንድ የመቆጣጠር ስራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እያስተላለፍን የጅግጅጋ ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ ሞጆ እና ቃሊቲ የሚገኙ የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም ክትትል በማድረግና በመያዝ የተሳተፋችሁ በየደረጃው የምትገኙ የፀጥታ አካላት እንዲሁም ጥቆማ በመስጠት ርብርብ ያደረጋችሁ የህብረተሰብ ክፍሎች የገቢዎች ሚኒስቴር ምስጋናውን ያቀርባል ፡፡

Related Post