አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ

ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ
ከፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የተሰጠ መግለጫ
የህወሃት ጁንታ ቡድን አባላት፣ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ)፣ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅንቄ (ጉህዴን) እና የኦነግ-ሸኔ አሸባሪዎች ተደራጅተውና ተቀናጅተው በጋምቤላ ክልል በጋምቤላ ከተማና በአካባቢው እንዲሁም በጊምቢና ደምቢ ዶሎ ከተማ በቅርቡ ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ ማድረጋቸውና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ከአካባቢው የፀጥታ ኃይል እና ህብረተሰብ ጋር በመቀናጀት በወሰዱት እርምጃ እኩይ ሴራቸው መክሸፉ ይታወቃል፡፡ ግብረ-ኃይሉ በወሰደው እርምጃ በርካቶች ማርኮ 137 የሽብር ቡድን አባላትን ደምስሷል፡፡

በዚህም በክልሉ የነበረው የፀጥታ ችግር በአሁኑ ወቅት ተወግዶ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ተደርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሽብር ቡድኖቹ ሽንፈታቸውን ለመቀበል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊንቢ ከተማ አካባቢ በሚገኝ ቶሌ ቀበሌ ላይ ሰላማዊ በሆኑና ምንም በማያውቁ ንፁሃን ህፃናትና ሲቪሎች ላይ ወዲያውኑ ዘግናኝ ጉዳት ማድረሳቸውና በርካቶችንም መግደላቸው ይታወሳል። ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታና ደህንነት አካላት የተውጣጣው የጋራ ግብረ-ኃይል ከሰኔ 07 እስከ ሐምሌ 07 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ዘመቻ ከ153 በላይ የሽብር ቡድኑ አባላትን ደምስሶ፣ ከዘጠኝ መቶ በላይ ማርኮና በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ ይገኛል፡፡

በዚህም ዘመቻ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ይጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች፣ ብዛት ያላቸው ጥይቶችና የጥይት መጋዘኖች፣ ወታደራዊ ትጥቆችና አልባሳት፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶችም ተይዘዋል፡፡

በሌላ በኩል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር አሸባሪ የጁንታ ቡድኑን ሲፋለሙ እና ለፀጥታ አካላቱ የኋላ ደጀን ሆነው እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ የፋኖ አባላት ዛሬ ላይ በክልሉ ለተገኘው ሰላምና ፀጥታ ድርሻቸውን ያበረከቱ ሲሆን ይህንን መልካም ተግባር አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

ሆኖም ፋኖን ሽፋን በማድረግ በህቡዕ የተደራጁት ጽንፈኛ የፋኖ አባላት ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ እና በህግ-ወጥ ተኩስ ሁከት ለማስፋፋትና ክልሉ ወደ ለየለት ብጥብጥ እንዲገባ ቢሞክሩም በፀጥታ ኃይሉ እና በክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ጥረት ሙከራው ሊከሽፍ ችሏል።

የፅንፈኛው ፋኖ ቡድን አባላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፖሊስ ተቋማት ዕውቅና ውጪ ወጣቶችን በመመልመል፣ በድብቅ በማሰልጠንና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ህዝቡ በፍርሀት እንዲሸበር ከማድረግ ባለፈ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በሚዲያ እያሰራጩ እንዲሁም የንፁሃን ዜጎችን ህይወት እያጠፉ፣ ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀሉና እየዘረፉ የነበሩ ከክልልና ከፌደራል የፀጥታ አካላት ከድተው የተያዙ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጣቸው፣ በቁጥጥር ስራ ሳይውሉ የቆዩ እና በግድያ ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ በጥቅሉ 5 ሺህ 804 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል።

ከዚህ ባሻገር በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በህቡዕ እየተሰባሰቡና እየተደራጁ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ከሚገኙ ውስን ፅንፈኛ የዲያስፖራ አባላት ጋር ተደራጅተውና ተቀናጅተው ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር ባሰባሰቡት ከፍተኛ ገንዘብ ትጥቅ በማሟላት፣ የጦር ሜዳ እና የሽምቅ ውጊያ ካርታ ስልጠና በመውሰድና ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በድብቅ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለማስገባት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር የሚገኙ ጽንፈኛ ሚዲዎችን በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ፣ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱና በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀምና መንግስትን በኃይል ለመጣል ሲያሴሩ በነበሩ ጽንፈኛ የፋኖ አባላት ላይ የአማራ ክልልና የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በጋራ ባደረጉት የተቀናጀ ኦፕሬሽን 14ቱ (አስራ አራቱ) በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ሚስጥራዊ ሰነዶቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል። በዚህም በክልሉ የነበረውም የፀጥታ ችግር በአሁኑ ወቅት ተወግዶ አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ተደርጓል።

በሌላ በኩል የጋራ ግብረ ኃይሉ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያው ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ወደ ከተማው ሰርገው በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 174 የህወሓት ጁንታ ቡድን አባላት፣ 98 የሸኔ ቡድን አባላት፣ 51 ጽንፈኛ የፋኖ አባላት፣ በከተማው ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ 100 ተጠርጣሪዎች እና 31 የአልሸባብና የአይ.ኤስ.ኤስ አባላትን በድምሩ 454 ተጠርጣሪዎች እግር በእግር በመከታተል ሊያደርሱት ያሰቡትን የሽብር ጥቃት እና ትርምስ ቀድሞ በማክሸፍ በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ 50 በተለያዩ የዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችም ከተለያየ የዘረፉት ንብረት ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል።

እስከአሁን የተገኘው ውጤትም ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ባደረገው ቀና ትብብር ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ የጀመረውን የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻውን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እያስታወቀ ህብረተሰቡ ጥቆማውንና ትብብሩን እንደተለመደው በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Related Post