አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰለ ቤኒሻንጉል ግድያ መግለጫ ሰጠ

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰለ ቤኒሻንጉል ግድያ መግለጫ ሰጠ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኮሚሽኑ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ አሳስበውታል፡፡

ኮሚሽኑ ከክልሉ ከመተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ አጳር ቀበሌ እንዲሁም ከወንበራ ወረዳ መልካን ቀበሌ እጅግ አሳሳቢ መረጃዎች እየደረሱት ነው፡፡ ኮሚሽኑ በጳጉሜ 1፤ 2012 ዓ.ም እንዲሁም ከጳጉሜ 2 አስከ መስከረም 3፤2013 ዓ.ም መካከል ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግስት ለማረጋጥ ችሏል፡፡

በቦታው ላይ ከሚገኝ አንድ መንግስታዊ ምንጭ መረዳት እንደተቻለው ቢያንስ በሁለት ዙር በደረሱ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጥ ችሏል፡፡

የክልሉ መንግስት እንደጠቆመው ከተፈናቃዮቹ መካከል 300 ያህል የሚሆኑት ወደ ቀያቸው የተመለሱ ሲሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር አካባቢውን ለማረጋጋት እየሰሩ ነው፡፡

ስለሆነም ኮሚሽኑ፡-

● በክልሉ ባልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የደረሱትን ጥቃቶች፣ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ሙሉ በሙሉ ያወግዛል

● በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሰራዊት፣በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት ያበረታታል

● በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ-መንግስትና እንዲሁም ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው የቃል ኪዳን ሰነዶች ማለትም፡ በአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ በአለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በሌሎች አግባብነት ባላቸው የሰብአዊ መብቶት ሰነዶች የተደነገጉትን በሕይወት የመኖር መብቶች እንዲከበሩ ይጠይቃል፤

● በክልሉ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ማጋጠማቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ገለልተኛ፣ ፈጣን እና ውጤታማ ምርመራዎችን በማካሄድ ግድያው በተከሰተባቸው ሁኔታዎች ላይ የጥፋተኞችን ተጠያቂነት እንዲያረጋግጡ ያሳስባል፤

● የሚመለከታቸው የክልሉ መንግስት አካላት ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ወደ ቀደመ ህይወታቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻቹ ጥሪ ያቀርባል፤

● ኮሚሽኑ በተለይም መሰረታዊ የሆነው በህይወት የመኖር መብት ይረጋገጥ ዘንድ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግስት አካላት እንዲሰሩ ያሳስባል፡፡

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች እና ባለድርሻ አካላት ገንቢ ውይይት እንዲያደርጉ እና ከማንኛውም ዓይነት የሁከት ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪውን ያቀርባል፡እንዲሁም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት እና ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለቻቸውን ሌሎች አግባብነት ያላቸውን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ የተቀመጡ መብቶችን እና ግዴታዎችን እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ እየጠየቀ፤ በቀጣይም ጉዳዩን በንቃት እንደሚከታተለው ይገልፃል፡፡

Related Post