አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

ቡና ባንክና ሰረገላ ገበያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

ቡና ባንክና ሰረገላ ገበያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ
ቡና ባንክና ሰረገላ ገበያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

ሰረገላ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር “ሰረገላ ገበያ” በሚል ስያሜ በአዲስ መልክ የጀመረውን በበይነ መረብ የታገዘ የግብይት ስርዓት በስራ ላይ አውሏል።

ይህ አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ስርዓት ህብረተሰቡ በሰረገላ ኩባንያ የበለጸገውን “ሰረገላ ገበያ” የተባለ የመሸመቻ መተግበሪያ በመጠቀም በቀላሉ የእለት ከእለት የፍጆታ እቃዎችን የሞባይል ስልኩን በመጠቀም በዱቤ ለመገበያየት ያስችለዋል። ቡና ባንክም በሰረገላ ገበያ የቀረበውን ቀላልና አመቺ የሸቀጦች መሸመቻ አማራጭ ለሚጠቀሙ ዜጎች የድህረ ሸመታ ክፍያ ብድር በማመቻቸት ሰፊ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የበይነመረብ ግብይት ስርዓት በዋናነት ዜጎች ግዜያቸውን ቆጥበው ቡና ባንክ በሚያቀርብላቸው የብድር ገንዘብ ከሰረገላ ገበያ የሚፈልጉትን የፍጆታ ዕቃዎች ባሉበት ሆነው በቀላሉ በማዘዝ እና ቤታቸው ድረስ እንዲመጣላቸው ለማድረግ የሚያስችላቸው ነው። ስምምነቱ ቡና ባንክ ለደንበኞችም የሸማቾች ብድር አቅርቦቶችን በማመቻቸት ቅድመ ሁኒታውን ያሟሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የፍጆታ ሸቀጦችን ከመተግበሪያው ላይ በቀላሉ ለማግኘት እና በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስርዓት ያለችግር ለመሸመት የሚያስችላቸው ይሆናል።

ሁለቱም ወገኖች የሸማቾች ብድር አቅርቦትንና የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አማራጩን በማስተዳደር ረገድ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በዚህ መሰረት ሰረገላ ኩባንያ የብድር አገልግሎት ለማግኘት ብቁ የሆኑ ተጠቃሚዎችን ለይቶ ከባንኩ ጋር በማገናኘትና አከፋፋዮች በባንኩ ሂሳብ እንዲከፍቱ እና ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ በማበረታታት ምቹ የገበያ ስርዓት እንዲፈጠር ያደርጋል።

ደንብና መመሪያዎችን በጠበቀ የአሰራር ስርዓት መሰረት የሰረገላ ገበያ መተግበሪያን በመጠቀም የዕለት ፍጆታ ሸቀጦችን ለመግዛት ፍላጎት ያለው ማንኛውም ዜጋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በማሟላትና የደንበኞች ብድር አገልግሎት ሒሳብ በመክፈት ያለምንም ቅድመ ክፍያ የሚፈልገውን ቁሳቁስ ከሰረገላ ገበያ ዶት ኮም [Seregelagebeya.com] ላይ በማዘዝ መግዛት ይችላል።

ሰረገላ ኩባንያም በዘረጋው የትራንስፖርት መረብ ሸማቾች የገዟቸውን ሸቀጦች ያሉበት ቦታ ድረስ የሚያደርስበት አሰራርን የሚከተል መሆኑም በስምምነቱ ላይ ተመልክቷል። ይህ በቡና ባንክ የድህረሸመታ ክፍያ ብድር አቅራቢነትና በይነመረብ ግብይት አማራጭ አቅራቢው ሰረገላ ኩባንያ ጥምረት የሚካሄደው የሸቀጦች ግብይት አማራጭ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ለሸመታ ወደገበያ የሚወጡበትን ጊዜ በመቆጠብ በትርፋማ ስራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ የሚያግዛቸው ይሆናል። በዋናነትም የገበያውን አማራጭ በመጠቀም በእጃቸው ገንዘብ ባይኖርም በፈለጉበት ጊዜ የሚፈልጉትን ሸቀጥ ለመግዛትና ክፍያውንም ከሸመታ በኋላ በሚቀመጥ የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመፈጸም ያስችላቸዋል።

ደንብና መመሪያውን የሚያሟሉ የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎች ‘ሰረገላ ገበያ’ የሚለውን መተግበሪያ ከጎግል ስቶር ወይም ከፕሌይ ስቶር በማውረድ የዲጂታል ገበያ ስርዓቱን መቀላቀልና አገልግሎቱን መጠቀም ይችላሉ። ቡና ባንክ የዜጎችን ጊዜና ጉልበት ቆጥቦ ለምርታማ ማህብረሰብ ግንባታ ለማዋል የሚያስችለውን ይህንን አዲስና ዘመናዊ የገበያ ስርዓት ከሰረገላ ገበያ ጋር በጥምረት መጀመር በመቻሉ እርካታ ይሰማዋል።

Related Post