አርእስተ ዜና
Thu. Dec 26th, 2024

በምርጫ የሚሳተፉ ሴቶችን ከጥላቻ ንግግር መከላከል ይገባል

በምርጫ የሚሳተፉ ሴቶችን ከጥላቻ ንግግር መከላከል ይገባል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) “መታገልን እንምረጥ” ወይም “Choose to Challenge” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የ2013 ዓ.ም. ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት ባስተላለፈው ጥሪ፣ በዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲ እጩነት፣ በመራጭነት፣ በምርጫ ፈጻሚነትና አስፈጻሚነት እንዲሁም በተለያየ መልኩ በምርጫው ሂደት የሚሳተፉ ሴቶች ጾታን መሰረት ላደረገ የጥላቻ ንግግር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲከላከሉ ጠየቀ።

ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሥርዓተ-ጾታ እኩልነት እና የሴቶች መብቃት ድርጅት (UNWOMEN) ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ በምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ ያደረገው ዳሰሳ፣ በተለይም በፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እና በሌሎች የምርጫ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉ ሴቶች በማኅበራዊ ሚድያም ሆነ በፊት ለፊት ለተለያዩ ጾታን መሰረት ላደረጉ የቃላት እና የአካል ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ያመለክታል።

በፌደራል ደረጃ በአዲስ አበባ፣ በአማራ፣ በኦሮምያ እና በሶማሊ ክልሎች ላይ ያተኮረው ዳሰሳ፣ በምርጫው ላይ በእጩነት፣ በመራጭነት፣ በምርጫ አስፈጻሚነት ተግባራት እና በሌሎች የፖለቲካ ተሳትፎ እንቅስቃሴ ያላቸው ሴቶች የተለያዩ ሥነልቦናዊ፣ አካላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ወሲባዊ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው ያሳያል። በፖለቲካ እና በምርጫ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩ ሴቶችን የግል ተሞክሮ እንዲሁም የፍትሕና የመንግስት አካላትን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻዎችን ልምድ ባካተተው በዚህ ጥናት መሰረት፣ በተለይ ሴት የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች ለእነዚህ ጥቃቶች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው።

ለዳሰሳው ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶቻቸውን መነጠቃቸውን፣ እስር፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ ከእምነት ቦታዎቻቸው መታገድ ጀምሮ እስከ በቤተሰብ መገለል ድረስ ለተለያዩ ችግሮች እንደተዳረጉ ያስረዳሉ። በተመሳሳይ መልኩ በማኅበራዊ ሚድያ እና በሌሎች ድረገጾች የፖለቲካ አቋማቸውን የሚገልጹ ሴቶችም ሆኑ በቀጥታ በምርጫው የሚሳተፉ ሴቶች በጾታቸው ላይ ላተኮሩ፣ በአካላዊ ቁመናቸው፣ በአለባበሳቸው ብሎም በማኅበራዊ ሕይወታቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ለሚያነጣጥሩ ዘለፋዎችና ሥነልቦናዊ ጉዳት ለሚያደርሱ የጥላቻ ንግግሮች ይጋለጣሉ። ይህን መሰል ጾታን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እንደ ጾታዊ ጥቃት የሚቆጠሩ ናቸው።

በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉ ሰዎች እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች የፍትሕና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተገለጸው ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች መፍትሔ የማይሰጡና በከፊልም እራሳቸው የችግሩ አካል እንደነበሩ ታይቷል። በመሆኑም ጥቃት የደረሰባቸው ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ተወዳዳሪዎች ከሚወክሉት ፓርቲ ወይም ከወዳጅና ዘመድ ውጪ የሚያማክሩትና የሚያበረታታቸው አካል እንዳይኖር አድርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ የሚወክሏቸው ፓርቲዎች እራሳቸው ለዚህ ጉዳይ አሳሳቢነት ቦታ አለመስጠታቸው አንዱ ችግር እንደነበረ ተገልጿል።

ይሁንና፣ በዳሰሳ ጥናቱ የተሳተፉና በተለያዩ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የተሰማሩ ሴቶች በሙሉ፣ ሴቶች የፖለቲካ አቋማቸውን በመግለጽም ሆነ በቀጥታ እጩነት ከመሳተፍ እራሳቸውን እንዳይገድቡ ይመክራሉ።

በምርጫ ወቅት በሴቶች የምርጫው ተሳታፊዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እና የጥላቻ ንግግሮች፣ ሴቶች በአንድ አገር የፖለቲካና የአስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው በኃይል እንደማገድ ስለሚቆጠር፣ አጠቃላይ የምርጫውን ተዓማኒነት እና ፍትሐዊነት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ። በመሆኑም “ለምርጫ 2013 ዓ.ም. ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ” በሚል ርዕስ ኢሰመኮ ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ባዘጋጀው ሰነድ ካካተታቸው ነጥቦች አንዱ “ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ግልጽ አመላካቾች ያሏቸውን ስልቶች በመንደፍ እንዲተገብሩ፣ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የምርጫው ሂደቶች በሙሉ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ” የሚጠይቅ ነው።

በተጨማሪም የሰብአዊ መብቶች አጀንዳው “ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በሁሉም የምርጫው ሂደት በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ፣ ጥላቻ እና ለመብት ጥሰት ምክንያት ከሚሆኑ ንግግሮች እና ተግባራት፣ በተለይም ከማናቸውም አይነት የኃይል እርምጃ ፈጽሞ እንዲቆጠቡ” ይጠይቃል።

“ለመታገል እንምረጥ” በሚል መሪቃል ታስቦ የሚውለውን የ2013 ዓ.ም. ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት፣ ኢሰመኮ በዘንድሮ ሀገራዊ ምርጫ በቀጥታ የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳውን በይፋ መቀበላቸውን ቃል እንዲገቡ እያስታወሰ፣ በተለያየ መንገድ በምርጫው ሚና የሚኖራቸው የሲቪል ማኅበረሰብና የመንግስት አካላት በተለይም በሴቶች የምርጫው ተሳታፊዎች ላይ የሚደርሱ ማናቸውንም ዓይነት ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንዲከላከሉ ጥሪ ያቀርባል።

Related Post