ኢትዮ ቴሌኮም ከሻንዶንግ ሃይ-ስፒድ ግሩፕ ኩባንያ ጋር ከፍተኛ አቅም ያለዉ የመረጃ ቋት (Hyperscale Data Center) መገንባትን በተመለከተ ስትራቴጂያዊ ውይይት አደረገ።
በዛሬው ዕለት ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የሻንዶንግ ሃይ-ስፒድ ግሩፕ ኩባንያ ጀኔራል ማኔጀር ካይ ኩን ከፍተኛ አቅም ያለው የመረጃ ቋት (Hyperscale Data Center) ግንባታን በተመለከተ የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት አድርገዋል። ሻንዶንግ የኢትዮጵያን ዲጂታል መሠረተ ልማት ለማሳደግ ያለመ ስትራቴጂያዊ አጋርነት በመፍጠር ከኩባንያችን ጋር በዳታ ማዕከል ግንባታ እና ፋይናንስ አቅርቦት ላይ ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል።
ይህም የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና የሚጫወት ከመሆኑ ባሻገር አስተማማኝ እና ሊሰፋ የሚችል የዲጂታል መሠረተ ልማት በማቅረብ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታውን ለማፋጠን ያስችላል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዕድገት ስትራቴጂውን ለመደገፍ እና #ዲጂታል_ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ያለመውን ራዕይ ለማራመድ ስልታዊ አጋርነቶችን መፈለጉን አጠናክሮ ቀጥሏል። እነዚህ አጋርነቶች የዲጂታል ስነ-ምህዳሩን ለመገንባትና ለማሳደግ፣ ዲጂታል አገልግሎቶችን ለማጎልበት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው።
በተተያያዘ ዜና ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ከሼንዜን ግሪንቴክ አርኤፍ ኮሚዩኒኬሽን ሊሚትድ ጋር የሀገራችንን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እውን ለማድረግ የሚያግዙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትና ለማልማት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ያካተተ ስትራቴጂያዊ የአጋርነት ስምምነት አደረገ።
ስምምነቱ፣ በዋና ስራ አስፈጻሚያችን ፍሬህይወት ታምሩና በሼንዜን ግሪን ቴክ አር ኤፍ ኮሚዩኒኬሽን ሊሚትድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ አቶ ሊዮ ካይ መካከል የኩባንያችን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተፈጸመ ሲሆን ሊዮ ካይ አፍሪካን ሲጎበኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ግሪንቴክ በቻይና አስር ግዙፍ ከሆኑ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን የኮሙኒኬሽን እና ዲጂታል ሶሉሽኖችን በማቅረብ አንጋፋ የሆነ ኩባንያ ነው፡፡