የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋችው ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ሉይጊ ዲማዮ ጋር ዛሬ ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓም በስልክ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ክቡራን ሚኒስትሮች በነበራቸው የስልክ ውይይት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው እና ኮቪድ 19ን በጋራ መግታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል። እንዲሁም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ መረጃ ተለዋውጠዋል።
ክቡር አቶ ገዱ ጣለያን የኢትዮጵያን ሪፎርም በመደገፍ እያደረገች ላለው የልማት እርዳታ አመስግነዋል። ኢትዮጵያ ከጣሊየን ጋር ያላትን ሀሉን አቀፍ ግንኙነትም ይበልጥ ለማጠናከር ትስራለች ብለዋል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ላይ በጠፋው የሰው ህይወት የተሰመቸውን ሃዘን የገለጹት ክቡር አቶ ገዱ ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመከለተም ገለጻ አድርገዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል ከዓለም አቀፉ ማህበረስብ እና ከጣሊያን ጋር በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥልም ክቡር አቶ ገዱ በዚህ ወቅት ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ እና ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን እያደረጉት ያለውን ውይይት በተመለከተም ክቡር አቶ ገዱ ለጣሊያኑ አቻቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል። የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር ሉይጊ ዲማዮ በበኩላቸው ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት እንደምትሰጥና ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመግታት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራና የምታደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ክቡር ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት አረጋግጠዋል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንበታ የሶስቱንም አገሮች ጥቅም በማከለ መልኩ በውይይት እንዲፈታ ጣሊያን ታበረታታለችም ብለዋል ክቡር ሉይጊ ዲማዮ በንግግራቸው።
(ምንጭ – የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር)