አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የኮንትሮባንድ አሉታዊ ጫና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ

የኮንትሮባንድ አሉታዊ ጫና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ
የኮንትሮባንድ አሉታዊ ጫና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ

በአዲሱ ገረመው – የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው አደጋ ሰፊ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ገለጹ፡፡ ከሪፎርሙ ወዲህ የችግሩን ግዙፍነት የሚመጠን አደረጃጀት እየተፈጠረ እንዳለና ባለፈው ዓመት ብቻ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች እንደተያዙም ተጠቁሟል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሸነር ደበሌ ቃበታ የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴን አስመልክተው በኢትዮጵያ ስላለው ነበራዊ ሁኔታ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ኮንትሮባንድ ከጤናማ የንግድ ሥርዓት የሚገኘውን ታክስ በከፍተኛ ደረጃ በመጉዳት ለአንዳንድ አካላት ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሀብት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በዚህም ኢኮኖሚያዊ አደጋው ሰፊ ሆኗል፡፡

በኮንትሮባንድና በሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት የማጭበርበሪያ ዘዴዎች በርካታ መሆናቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በተለይ በድንበሮች ስፋት ምክንያት የሚካሄደው ኮንትሮባንድ ሰፊ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እነዚህ አካላት ከፍተኛ የሆኑ የፍጆታ እቃዎችን፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ የምግብ ፍጆታዎች፣ መለዋወጫዎች፣ መድኃኒቶች፣ ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦች፣ በከፍተኛ ደረጃ ባላቸው ግንኙነቶች ሁሉ ወደ ሀገሪቷ ለማስገባት እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግዶች የሚያደርሱት ሀገራዊ ጫና ከፍተኛ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በኢትዮጵያ ባለው ነበራዊ ሁኔታ ችግሩን አቅልሎ ዜሮ ማድረግ ባይቻልም ትልቅ የክትትል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።

ባለፉት የሪፎርም ዓመታት አደጋውን ለመከላከል የተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች የሚበረታቱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑና የገቢዎች ሚኒስቴር ይህንን በመከታተል ረገድ የተለየ ሥምሪትና ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

“የችግሩን ግዙፍነት የሚመጥን አደረጃጀት ያስፈልጋል። በሰው ኃይል ቁጥርና በስምሪት ታክቲኩ በአሰራር ሥርዓቱም በቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግ ይፈልጋል። በዚህ ደረጃ መሠረታዊ ሥራዎች ተሰርተዋል። ተጨባጭ እርምጃዎችም ተወስደዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የተለያዩ ቁሳቁሶች ተይዘዋል” ነው ያሉት።

በችግሩ ስፋት ምክንያት ከሪፎርሙ ወዲህ አደጋውን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ከፍተኛ መሆናቸውንና በየጊዜው የሚያዙ የኮንትሮባንድ እቃዎች በርከታ መሆናቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነር ደበሌ፤ ከችግሩ ለመውጣት በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የተቀመጠውን የፀረ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ግብረ ኃይል የሚመራበትን ስትራቴጂ በሚገባ ተግባራዊ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ምንጭ፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Related Post