በአዳማ፣ በደብረ ብርሃን፣ በድሬዳዋ፣ በባሕር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በመቀሌ እና በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰው ሃይል አቅርቦትን በማሻሻል የሥራ ዕድል እና ቅጥር እንዲኖር ለማድረግ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና በፈርስት ኮንሰልት መካከል ስምምነት ተፈረመ፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ትናንት ስምምነት በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ እንደገለፁት፤ ኢንቨስተሮችን መሳብ ብቻ ሳይሆን ለኢንቨስተሮችም ምቹ ሁኔታን መፍጠር ዋነኛው አማራጭ ነው።
ኢንቨስተሮች እዚሁ ቆይተው ያላቸውን ቴክኖሎጂ እና ውጤታማነት ለኢትዮጵያ እንዲያሸጋግሩ ማድረግ፤ በኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ የውጪ አምራች ኢንቨስተሮች ከአገር በቀል አምራች ባለሃብቶች እንዲሁም ከጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ግብአት እንዲያገኙ የማስተሳሰር ሥራ ለመስራት ስምምነቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
በማስተርካርድ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ የተዘጋጀው የብሪጅስ ፕሮግራም የተቀረፀው ኢንቨስት መንትን ውጤታማ ሊያደርግ በሚችል መልኩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንቨስተሩም ደስተኛ እና ውጤታማ ሆኖ በፊት ኢንቨስት ካደረገው በላይ አስፋፍቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ እና እንዲቆይ የሚያስችል ፕሮግራም ነው ብለዋል።
ኮምሽነሯ፤ስምምነቱ ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ሰራተኞችን ከመመልመል እና ከማሰልጠን በተጨማሪ የአገር ውስጥ ባለሃብትን ከመደገፍ አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ የሚታመን መሆኑን ገልፀዋል። በመንግሥት በለሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በግል በለሙት በአጠቃላይ ከ75ሺህ በላይ ሠራተኞች መኖራቸውን ገልፀው፤ በሠራተኞቹ ከሚቀርቡ የተለያዩ ጥያቄዎች መካከል ስልጠናዎችን የማግኘት እና የመኖሪያ ቤት ችግር ተጠቃሾች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ፕሮግራሙ የሥልጠናውን ችግር ይፈታዋል ተብሎ ይታመናል ያሉት ኮሚሽነሯ፣ ከ100 ኪሎ ሜትር ክበብ (ራዲየስ) የሚመጡ ሰራተኞች የቤት ችግራቸውን ለማቃለል፤ ራሱ ባለሃብቱ ቤት እንዲያቀርብ፤ በሌላ በኩል ከማህበረሰቡ ጋር በማስተሳሰር የቤት አቅርቦትን ለመጨመር ጥረት ተደርጎ በቦሌ ለሚ 4ሺህ ሠራተኞች ቤት ተገንብቶላቸዋል ብለዋል። ባለሃብቶቹ በአዳማ እና በድሬዳዋም ለመስራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው፣ በሐዋሳም መሬቱን ተረክበው ቤቱን ለመገንባት ተነሳሽነት እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግሥት ዜጎች በኢንዱስትሪው ሥራ ላይ ሲሰማሩ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ በማገዝ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ታታሪ በሚል በንግድ ባንክ የሂሳብ ደብተር እንዲከፍቱ በማድረግ ለ3ዓመታት ከቆጠቡ በኋላ ወደ ራሳቸው ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በበዓላት ጊዜ እንዲሰሩ እና ውጤታማ ሲሆኑ ማበረታቻ (ቦነስ) እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንጠቅሰው፣ በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ብሪጅስ ፕሮግራም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ኮሚሽነሯ አመልክተዋል።
የብሪጅስ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ሚካኤል አዲሱ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ብዙሃኑ ህዝብ ወጣቱን ጨምሮ ግብርና ላይ የተሰማራ በመሆኑ በሰዓት መግባት መውጣት፣ ከሌሎች ሠራተኞች ጋር እየተቀባበሉ መስራት፣ በሰዓት ማስረከብ እና ጥራቱን ጠብቆ ተወዳዳሪ ሥራን መስራት ለሠራተኛው በሚያስገኘው ጥቅም ላይ ግንዛቤ የለም።
በዚህ ሳቢያ የሠራተኞቹም ተወዳዳሪነት እና የፋብሪካዎችም ውጤታማነት አደጋ እያጋጠመው ነው። ሠራተኞች የጠበቁት እና የሚያገኙት የተለያየ ሲሆን፣ ስራውን እየለቀቁ፤ ቀጣሪውም ሆነ ተቀጣሪው እየተጎዱ ይገኛሉ ሲሉ አብራርተዋል። ‹‹ይህ ቀላል ቢመስልም ከፍተኛ ክፍተት የፈጠረ ነው፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ለተቀጣሪዎች ‹‹ኢንዱስትሪ ፓርኩ እነዚህ ነገሮች ከእናንተ ይጠብቃል። በዚህ መሰረት ትሰራላችሁ፡፡›› በሚል በቂ መረጃ ተሰጥቶ አሳውቆ ወደ ስራው የማምጣት ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
እንደአቶ ሚካኤል ገለፃ፤ መረጃውን የሚያውቅ ሥራው ላይ የመቆየት እና ምርታማ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ ይሆናል። አምጥቶ ማስቀጠር ብቻ ሳይሆን ከተቀጠሩ በኋላ ሥራ ላይ እያሉ የኢትዮጵያ እና የውጪ አሰሪዎች ባህል የተለያየ በመሆኑ፤ ከውጪ ተቋማት ጋር በምን መልኩ መግባባት እንደሚገባ በተግባር ሥልጠና ይሰጣል። በጣም ለስራው አስፈላጊ የሆኑ የሥራ ሥነምግባርን በሚመለከት ስልጠናዎች ወጥ በሆነ መልኩ የሚሰጥ ሲሆን፤ ተቀጣሪዎች ገቢያቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸውም እንዲሁ የሚገለፅላቸው ይሆናል፡፡
ስልጠናው በክፍል ውስጥ በአንድ ጊዜ ማስተማር ሳይሆን ቀጣይነት ባለው መልኩ ድጋፍ እና ስልጠና እየተሰጠ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረው፣እነርሱን ብቁ በማድረግ ዘመናዊ ከሆነው ኢንዱስትሪ ጋር የማስተዋወቅ እና በስራቸውም ደስተኛ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። ሥራው ቀጣይነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው፣ በሁሉም ኢንዱስትሪዎች ላይ እንዲተገበር ስርዓት ይገነባል ብለዋል።
ከመንግሥት ፣ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በተጨማሪ ከኢንቨስተሮች ማህበር ጋር በመተባበር ሥርዓቱ በሚያመች መልኩ ቀጣይ ሆኖ የሚዘረጋ መሆኑን አቶ ሚካኤል ጠቁመዋል።
በሰባት ፓርኮች ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ስርዓቱን ዘርግቶ በዘላቂነት ስልጠናውን ለማስቀጠል 20 ሚሊየን ብር በጀት መያዙ ተጠቁሟል፡፡እንደ አስፈላጊነቱ ለፕሮግራሙ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል። ብሪጅስ ፕሮግራም የአምስት ዓመት ዕቅድ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ ዕድል ፈጠራ ለ300ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶች ሥልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል።
(ምንጭ – አዲስ ዘመን መስከረም 13/2013)