አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

የትግራይ የውሃ ስርአትን ወደ ነበረበት መመለስ

የትግራይ የውሃ ስርአትን ወደ ነበረበት መመለስ
የትግራይ የውሃ ስርአትን ወደ ነበረበት መመለስ

’እኔ የውሃ ሰው ነኝ” ይላል በኢትዮጵያ ድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን (ኤም.ኤስ.ኤፍ)ውስጥ መሐንዲስ እና የውሃ እና ሳኒቴሽን ባለሙያ በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኘው ወልደኪሮስ አሰፋ፡፡ “በኤም.ኤስ.ኤፍ ውስጥም ጥሩ ስራ አለኝ’’ በማለት ይናገራል፡፡

ወልደኪሮስ በኤም.ኤስ.ኤፍ. በተደረገ ድጋፍ 600 የእጅ ፓምፖች በድጋሚ ጥገና እየሰሩ ባሉበት በትግራይ ክልል፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በምትገኝ ማይ-ከዋኢት በምትባል ትንሽ መንደር የውሃ ፓምፖችን እየፈተሸ ይገኛል። ጥገናው በሁለት አመት ጦርነት ምክንያት በውሃ እጦት የተሰቃየውን ክልል የውሃ አቅርቦት ወደ ነበረበት ለመመልስ እረድቷል።

“ጦርነቱ እየተፋፋመና አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ ሲመጣ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአንድ ሳምንት ያህል ወደ ጫካ ሸሽተው ነበር” ሲል ወልደኪሮስ ያስረዳል፡፡ ‘’ነዋሪዎቹ ወደ ቄሄያቸው ሲመለሱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ አብዛኞቹ ለመጠጥ ውሃ የሚገለገሉባቸው የእጅ ፓምፖች ተሰባብረው በድንጋይ ተሞልተው ነበር፡፡” የእጅ ፓምፖቹ በአካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሀ ብቸኛ አማራጭ ነበሩ፡፡

ሁኔታው ለማይ-ከዋአቲ ህዝብ ውሃ ለመቅዳት 1.5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደ ሚገኝ ወንዝ ከመሄድ ውጪ ምንም አማራጭ አልሰጠውም። በዚህም ሳቢያ ብዙዎች ለተቅማጥ ህመም ተጋልጠዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የሚያገኙትን ማንኛውንም ውሀ ለመጠጥና ለምግብ ማብሰያነት እና ለመጠጥ እንጂ ለመታጠብ ባለመሆኑ ለቆዳ በሽታ እና ለሌሎች በንፅህና ጉድለት በፍጥነት ለሚዛመቱ በሽታዎች የመጋለጥ እድልም ከፍተኛ ነበር::

የኤም.ኤስ.ኤፍ ወደ ትግራይ መመለስ
ኤም.ኤስ.ኤፍ በህዳር 2015 ዓ.ም ወደ ትግራይ ሲመለስ ክልሉ ከሁለት አመት አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ገና በማገገም ላይ ነበር። በጥገና እጦት፣ ወይም ሆን ተብሎ በተቃጣ ጥፋት፣ አልያም በውጊያው ምክኒያት በመሰረተ ልማቶች ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ የጤና ተቋማት እምብዛም አገልግሎት አይሰጡም።

ኤም.ኤስ.ኤፍ ቅድሚያ ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የጤና ተቋማትን የውሃ ስርዓት ማደስ እና አገልግሎት መስጠት የቆሻሻ አወጋገድ ስረትን እንደገና ማስተካከል ነበር።

ለምሳሌ የኤም.ኤስ.ኤፍ ቡድን የሽሬ ስሑል ሆስፒታል ንጹህ ውሃ እንዲያገኝ ማድረግ የቻለ ሲሆን በተጨማሪም መጸዳጃ ቤቶችን፣ የገላ መታጠቢያ እና የማጠቢያ ቦታዎችን ገንብቷል። ቡድኑ ከዚህም በተጨማሪ የህክምና ቆሻሻዎች በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወገዱ ለማስቻል እንደ መርፌ፣ የቆሸሹ ልብሶች፣ ስለታምና መሰል አላስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማስወገጃ ስፍራዎችን ገንብቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ቡድኑ ከተቋሙ አቅራቢያ ያለና አደገኛ የሆኑ የተወገዱ የህክምና ቆሻሻዎች የያዘ የቆሻሻ ቁልልን አጽድቷል።

የኤም.ኤስ.ኤፍ ሌላው ዋነኛ ግብ የነበረው የውሃ ወለድ በሽታ የሆኑትን እንደ አጣዳፊ ተቅማጥ፣ እንዲሁም በጥገኛ ተውሳኮች የሚከሰቱትን የቆዳ እና የአይን በሽታዎች ለመከላከል ይቻል ዘንድ ንፁህ ውሃ ለነዋሪዎች ማቅረብ ነበር፡፡ ትልቁ ስጋት የነበረው በንፁህ ውሃ አቅርቦት እጦት የኮሌራ ወረርሽኝ እንዲከሰት ምክኒያት ሊሆን ይችላል የሚለው ነበር።

የንጹህ ውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ አለመኖር የሚያስከትሏቸው የጤና መዘዞች፡
በያዝነው አመት ከታህሳስ እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ በሰሜን ምዕራብ እና በማዕከላዊ ትግራይ የተደረጉ በርካታ ግምገማዎች እንደሚያሳዩት በ14 ወረዳዎች ውስጥ ከሚገኙ 2000 ከሚሆኑ በእጅ የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች በስራ ላይ የነበሩት 34 በመቶው የሚሆኑት ብቻ ናቸው።በዝናብ ወቅት የውሃ ምንጮች ሊበከሉ ስለሚችሉ እና የኮሌራ ወረርሽኝ የመከሰት እድልን ስለሚጨምር የተበላሹ ፓምፖችን መጠገን በጣም አስፈላጊ ነው።

የውሃ ፓምፖች አገልግሎት በማይሰጡበት ጊዜ ሰዎች ከሐይቆች እና ከወንዞች ውሃ ይጠቀማሉ፡፡ እነዚህ የውሀ ምንጮች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ንጽህናቸው ያልተጠበቀ ነው፡፡ “በአንድ ወቅት፤ በመጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ በትግራይ ከምናያቸው ከአራት ታማሚዎች ውስጥ አንዱ መከላከል በሚቻል የውሃ ወለድ በሽታ ይሰቃይ ነበር” በማለት በኢትዮጵያ የኤም.ኤስ.ኤፍ የህክምና አስተባባሪ ሳምሪን ሁሴን ይናገራሉ።

በሚያዝያ ወር መጨረሻ ከሸራሮ በስተደቡብ በምትገኝ ዴርሶ በተባለች ትንሽ መንደር አንድ የአስር ዓመት ልጅ ወደ አካባቢው ጤና ጣቢያ ሲሄድ ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ በርካታ የአጣዳፊ ተቅማጥ ተጠቂዎች ተመዝግበዋል። “በመንደሩ ውስጥ ያለው ሁኔታ በጣም ጥሩ አልነበረም፡፡” ይላል በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ከገመገመው ቡድን መካከል አንዱ የሆነው የኤም.ኤስ.ኤፍ የውሃ እና ሳኒቴሽን ተቆጣጣሪ ዳንኤል ሽሞንዲ፡፡“የውሃ ጉድጓዶች አልነበሩም። ሰዎች ከወንዙ የሚወጣውን ውሃ ለሁሉም ዓላማ ይጠቀሙ ነበር። በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በባዶ ሜዳ መፀዳዳት የተለመደ ተግባር ነበር”

በምላሹም ቡድኑ ለ120 አባወራዎች የውሃ ማጣሪያ መድሃኒቶችን ያከፋፈለ ሲሆን በመንደሩ ውስጥ ሌሎች ሰዎች መታመማቸውንም ለማረጋገጥም ሞክሯል። በዚህም ህይወቱ ያለፈው ታዳጊ ሁለት ወንድም እና እህቶች በከባድ ተቅማጥ ተጠቅተው የተገኙ ሲሆን ከዚያም በሸራሮ በኤም.ኤስ.ኤፍ እርዳታ የኮሌራ ወረርሽኝን ለማከም ወደ ተገነባው ማእከል እንዲገቡ ተድርጓል። ይህ ክስተት ከአካባቢው በመኪና የሁለት ሰአት ርቀት ላይ የሚገኘውንና የክልሉ ሪፈራል ተቋም የሆነውን ሱሁል ሆስፒታልንም የኮሌራ ወረርሽኝ ህከምና ላይ እንዲሰራ መንስኤ ከመሆኑም ባሻገር ሆስፒታሉ የኮሌራ ማከሚያ ማዕከሉን በማደስ ወረርሽኙ በሚከሰትበት ጊዜ ምላሽ የመስጠት አቅማቸውንም ለማጠንከር ባለሙያዎቹንም አሰልጥኗል።

የማያቋርጥ የጸጥታ ችግር የውሃ መሠረተ ልማት መልሶ ግንባታን ይጎትታል
በማለዳው አዲሳለም ከኤርትራ ድንበር ላይ በምትገኘው አደመይቲ መንደር ውስጥ የእጅ ፓምፕ ለመጠገን የሚያስፈልገውን መለዋወጫ በግመሉ ላይ ይጭናል “አብዛኛው ነዋሪ እስካሁን ከዚህ አካባቢ አልተመለሱም” ይላል አዲስአለም፡፡ “ብዙዎች አሁንም በተፈናቃይ ጣቢያዎች ውስጥ ወይም ከዚሁ የአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ተጠልለው ይኖራሉ”

ከጦርነቱ መቆም በኋላ ቋሚ የጸጥታ ስጋት ቀንሷል። ሆኖም ብዙ ወጪ ወጥቶበት ተደጋጋሚ ጥገና የተደረገለት የትግራይ የውሃ መሠረተ ልማት ተዘርፏል አልያም ሆን ተብሎ እንዲወድም ተደርጓል፡፡

የረድኤት ድርጅቶች አዳዲስ እና ትላልቅ ድጋፎችን ለማድረግ ሲያመነቱ ቆይተዋል። ለሸራሮ ከተማ ንፁህ ውሃ የሚያቀርቡ የውሃ ማጣሪያ ፓምፖችን ለመተካት ስድስት ወራት ፈጅቷል። በዚያን ጊዜ በከተማዋ ውስጥ በጭነት መኪና ወይም በአህያ ውሀ እየጫኑ ለሚያቀርቡ ምስጋና ይሁንና ነዋሪው በህይወት ሊቆይ ችሏል፡፡ በተጨማሪም ኤም.ኤስ. ኤፍ በየቀኑ እስከ 1.4 ሚሊዮን ሊትር ንፁህ ውሃ ለስድስት የተፈናቃይ ካምፖች አቅርቧል።

የውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ቴክኒሻኖች በማይኖሩበት ጊዜ፣ የኤም.ኤስ.ኤፍ ቴክኒሻኖች ጥገናውን በቀጥታ በማድረግ ጎን ለጎን በውሃ አስተዳደር የተቀጠሩ አዳዲስ ሰራተኞችንም አሰልጥነዋል። ዓላማው ተጎድተው የነበሩትን የእጅ ፓምፖች መልሶ መጠገን እና ወደስራ ማስገባት ላይ በንቃት መሳተፍ ነው። በትግራይ ከመልሶ ግንባታው ጎን አንዳንድ አካባቢዎች የንፁህ ውሃ አቅርቦትን ለማሳደግ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና ሁኔታዎችን ለማሻሻል ተጨማሪ ግብአት እና ጥረት ያስፈልጋል።

– ማጠቃለያ –
እ.ኤ.አ. ሰኔ 2021 ባልደረቦቻችን ማሪያ ሄርናንዴዝ ማታስ፣ ቴዎድሮስ ገብረማርያም ገብረሚካኤል እና ዮሃንስ ሃለፎም ረዳ በግብረ-ሰናይ ሰራተኞች መሆናቸው በግልፅ እየታወቀ በትግራይ ክልል በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ውይይት ብናደርግም በእለቱ በባልደረባዎቻችን ላይ ስለደረሰው ነገር ምንም አይነት ተዓማኒነት ያለው ምላሽ አላገኘንም። ኤምኤስኤፍ ለሞታቸው ተጠያቂነትን ለማስፈን ሁሉንም አማራጮች መጠቀሙን ይቀጥላል። ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ የግብረሰናይ ድርጅት ሰራተኞችን ደህንነት ለማሻሻል አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ተስፋ እናደርጋለን።

ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን ወይም ኤም .ኤስ. ኤፍ. በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 37 ዓመታት በግጭት ወቅትና እንደ ድርቅ እና ጎርፍ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም እንደ ኩፍኝ ወይም ኮሌራ በመሳሰሉ ወረርሽኞች ለተጎዱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች በአከባቢ፣ በክልል እና በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ሲሰጥ ቆይቷል። አፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ትግራይ እና ሶማሌ ክልልን ጨምሮ በኢትዮጵያ ከ11 ክልሎች በ7ቱ ውስጥ ለሚገኙ ማህበረሰቦች የህክምና እና ሰብአዊ እርዳታ እየሰጠ ይገኛል። እንዲሁም ላለፉት 20 አመታት በአማራ ክልል አብዱራፊ ወይም ምድረ ገነት በሚባለው አካባቢ የእባብ ንድፊያ እና በካላዛር በሽታ የተጠቁ ሰዎችን ለማከም እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። ሁሉም ተግባሮቻችን በሰብአዊነት፣ በነፃነት፣ ገለልተኛነት እና ባለማዳላት መርሆዎች ይመራሉ::

የኤዲተሩ ማስታወሻ ይህ ጽሁፍ ተዘጋጅቶ የቀረበው በኤም .ኤስ. ኤፍ. ኢትዮጵያ ነው።

Related Post