ከዛሬ ጀምሮ ንብረት በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደማይቻል የፌዴራል ሰነዶች መረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የብር ኖቶችን ለውጥ ተከትሎ ከዛሬ መስከረም 7 ቀን 2013 ጀምሮ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው የሚመጡ ተገልጋዮች የሽያጭ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ አከፋፈልን በተመለከተ ክፍያው መፈጸም ያለበትን መንገድ ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል።
በሽያጭ ውል ጊዜ የሽያጭ ዋጋው ባንክ ከሚገኝ የገዢ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት፡፡
የኤጀንሲው የአሰራር ማሻሻያ ከታች በቀረበው መልኩ መሆኑ ተግልጿል። የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል እንዲሁም የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ኤጀንሲው የሚመጡ ተገልጋዮች የሽያጭ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ አከፋፈልን በተመለከተ ክፍያው መፈጸም ያለበት፡-
• በሽያጭ ውል ጊዜ የሽያጭ ዋጋው ባንክ ከሚገኝ የገዢ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት፡፡
• በብድር ውል ጊዜ የብድሩ ገንዘብ ባንክ ከሚገኝ የአበዳሪ ሂሳብ ተቀናሽ ሆኖ ወደ ተበዳሪ የባንክ ሂሳብ የተላለፈ (Transfer) መሆን አለበት፡፡
በመሆኑም የሽያጩ ዋጋ ወይም የብድሩ ገንዘብ ክፍያው ከላይ በተገለጸው አግባብ የተፈጸመ ስለመሆኑ የሚገልጽና በባንኩ ማህተም የተደገፈ የሂሳብ ማስተላለፊያ (Bank Transfer Slip) የሰነድ ማስረጃ መቅረብ ያለበት መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
በተጨማሪም ህገወጥነትን ለመከላከል ሲባል ሌሎች የአሰራር ማሻሻያዎች እስኪደረጉ ድረስ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀ ንብረትን በስጦታ የማስተላለፍ ውል አረጋግጦ የመመዝገብ አገልግሎት ኤጀንሲው ላልተወሰነ ጊዜ የማይሰጥ ይሆናል፡፡