አርእስተ ዜና
Sat. Nov 23rd, 2024

ተመሳስለዉ የተሠሩ አዲሶቹ የብር ኖቶች በባሕር ዳር ተያዙ

ተመሳስለዉ የተሠሩ አዲሶቹ የብር ኖቶች በባሕር ዳር ተያዙ
ተመሳስለዉ የተሠሩ አዲሶቹ የብር ኖቶች በባሕር ዳር ተያዙ

በባሕር ዳር ከተማ ከየት እንደታተመ ያልታወቁ ከአዲሱ የገንዘብ ኖት ጋር የሚመሳሰሉ የባለአንድ መቶ እና ሁለት መቶ የብር ኖቶች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ሰዎች ሆን ብለውም ይሁን ባለማስተዋል ከገንዘቦቻቸው መካከል ተመሳስለው የታተሙ የገንዘብ ኖቶቹን ይዘው በመገኘታቸው በሕግ ቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የባሕር ዳር ቋሚ ምድብ የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምሪያ ዐቃቢ ሕግ ማርይሁን ይታየው በባሕር ዳር ከተማ ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ተመሳስሎ የተሠራ የአዲሱ የገንዘብ ኖት ብር ሲጠቀሙ የተገኙ ሁለት ሰዎች በፍርድ ቤት ቀላል እስራት ቅጣት እንደተላለፈባቸው አስታውሰዋል፡፡ ሕዝቡ አዲሱን የገንዘብ ኖት ባለማወቅ ለሚፈጠርበት የሕገ ወጥ ገንዘብ ግብይት ከሕግ ተጠያቂነት እንደማይድን ተረድቶ ሊገዛና ሊሸጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ሆን ተብሎ ተመሳስሎ የተሠራ ገንዘብ ሲያዘዋውር የተገኘ እና የወንጀሉ ምንጭ የሆኑ ሰዎች እስከ 15 ዓመታት እሥራትን ጨምሮ ያፈሩትን ሀብት ንብረት ሁሉ የሚያስወርስ ወንጀል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዚህ ወቅት የሀገሪቱ ከፍተኛ የገንዘብ ኖት የሆኑት የ200 እና የ100 የብር ኖቶች ተመሳስለው መታተማቸውን ማረጋገጡን የተናገሩት ዐቃቢ ሕጉ ‘‘አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመሳስለው የቀረቡ ገንዘቦች መግባታቸው ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት አስጊ ነው’’ ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ተመሳስለው የቀረቡ ገንዘቦች ገበያውን የሚያስወድዱ እና ለሕገ ወጥ ድርጊቶች ምንጭ መሆናቸውን ተገንዝቦ ከባለሙያዎች ቀርቦ በመረዳት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ስለአዲሱ የገንዘብ ኖት ባሕሪ በቂ የመገናኛ ብዙኃን የግንዛቤ መስጫ መርሐ ግብሮች፣ በከተማና በገጠር ዋና ዋና ቦታዎች የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችንና ለመከላከያ ተግባሩ የተንቀሳቃሽ የቅስቀሳ ስልቶችን በመጠቀም ማስገንዘብ የመንግሥት እና የባንኮች ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አቶ ማርይሁን ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ሀገሪቱ የገንዘብ ኖት ለውጥ ማድረግ ከተገደደችባቸው ምክንያቶች አንዱ የሆነውን የሕገ ወጥ ገንዘቦች መከማቸት እና ከባንክ ውጪ መንቀሳቀስ ያስከተለውን የዋጋ ግሽበት እና የምጣኔ ሀብት መግሪያነት ግብ ያሳጣል፡፡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመሳስሎ የቀረቡ የብር ኖቶች በፍጥነት ከባንክ ገበያ ውጪ የአገልግሎት እና የሠራተኛ ገበያ ውስጥ በማግባታቸው የነበረውን ችግር መልሶ እንዲያንሠራራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑም እየተመላከተ ነው፡፡

የአብክመ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታዘባቸው ጣሴ በአዲሱ የገንዘብ ኖት ሽግግር ጊዜ ሕገ ወጥ ገንዘብ እንዳይስፋፋ ሕዝቡ ስለአዲሱ ገንዘብ በቂ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ ወደባንክ ሲሄድ እና ሲገበያይ ትክክለኛው የገንዘብ ኖት መሆኑን አውቆ ሊሆን እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ታዘባቸው ‘መንግሥት የሕገ ወጥ ገንዘቦችን ምንጭ ለማድረቅ ጠንካራ ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነቱ ሕዝቡ ስለአዲሱ የገንዘብ ኖት በበቂ ተርድቷል ብለው እንደማያምኑ ተናግረው መንግሥት የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ስለአዲሱ የገንዘብ ኖት ለሕዝብ ሊያሳውቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡ ሕገ ወጥ ገንዘብን ይዞ መገኘትና መገበያየት ሊያስጠይቅ የሚችል መሆኑን አውቆ በአዲሱ የገንዘብ ዝውውር ዕውቅና ማነስ ምክንያት የሚፈጠሩ ብዥታዎችን በመጠቀም ሊከብሩ የሚያስቡ ሕገ ወጦችን ሊከላከል እና ሊጠቁም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
(ምንጭ – የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ነው)

Related Post