በደቡብ ክልል ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የወጡ ክልከላዎችን የተላለፉ 7 ሺህ አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ።
ለህዝቡ ደህንነትና ስጋት የሚፈጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ጠበቅ ያለ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድም ገልጸዋል። አቶ ርስቱ በመግለጫቸው እንዳመለከቱት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ የወጣውን አዋጅና ክልከላዎች ጥሰው የተገኙ አሽከርካሪዎች እንዲቀጡ ተደርጓል።
ሰዎቹ የፊት መሸፈኛ ጭምብል ባለማድረግ፣ ከተፈቀደላቸው የሰው ቁጥር በላይ በመጫንና ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ በመያዛቸው ቅጣት ተላልፏባቸዋል ብለዋል። ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከማስተማር ጎን ለጎን በአሽከርካሪዎች ላይ በተወሰደው ህግ የማስከበር ርምጃ 8 ሚሊየን ብር ተቀጥተዋል።
“ህዝብን በመልካምነት ማገልገል ዋጋው ከገንዘብ በላይ ነው” ያሉት አቶ ርስቱ ህግ የማስከበር ስራው የተሳፋሪዎችን ብቻ ሳይሆን የረዳትና የሾፌሮችን ህይወት ለመታደግ ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል። ግማሽ ተሳፋሪ ከጫኑ ክፍያው እጥፍ እንዲሆን ህግ መውጣቱን ጠቅሰው በተለይ አዋሳኝ ከሆነው ኦሮሚያ ክልል ጋር የተጣጣመ ህግ እንደወጣ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
(ምንጭ – ኤፍ ቢ ሲ)