አርእስተ ዜና
Wed. Dec 25th, 2024

ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት የአፋር ክልል ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል

ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት የአፋር ክልል ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል
ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት የአፋር ክልል ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል

የአፋር ክልል ህዝብ ከአንድ ዓመት በላይ በቆየው አስቸጋሪ ሀገራዊ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር ፈተናዎችን በመጋፈጥ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቷ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በሰመራ ከተማ እየተወያዩ ነው። በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ከአንድ ዓመት በላይ በቆየው አስቸጋሪ ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ የአፋር ክልል ህዝብ ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት መከበር ፈተናዎችን በመጋፈጥ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። በዚህ ሂደት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ንጹሃን ዜጎች ህይወት ጠፍቷል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት ማስከተሉን፤ በተለይም ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም አቅመ ደካሞችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን ተናግረዋል። ችግሩ በውይይትና በመግባባት እንዲፈታ ድርጅታቸው የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።
በተጨማሪም ድርጅቱ አፋርን ጨምሮ በሀገሪቱ በጦርነቱና ተያያዥ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ እንዳሉት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት አጋር በመሆን በክልሉ ለተገኙ እድገትና ማህበራዊ መሠረተ ልማቶች መስፋፋት የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ሆኖም አሸባሪው የህወሃት ቡድን በክልሉ በፈጸመው ወረራ ምክንያት የህብረተሰቡ ኑሮ እየተመሠቃቀለ መሆኑን ገልጸው፤በዚህም የሽብር ቡድኑ ንጹሃን አርብቶ አደሮች ላይ ግድያና ጥቃት እንደሚፈጽም ጠቁመዋል። ቡድኑ ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም አቅመ ደካሞች ላይ በከባድ መሳሪያዎች በአበአላ፣ ኢረብቲ፣ መጋሌ፣ በራህሌና ኩነባ አካባቢዎች ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የህብረተሰቡ የኑሮ መሰረት የሆኑ ግመልና የተለያዩ እንስሳትን ከመግደል ሌላ የጤናና የትምሀርት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች እያወደመ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በክልሉ 21 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ አርብቶ አደሮች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ከነዚህም ውስጥ ከ600 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፣ የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድና የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ዛሬ ሠመራ ከተማ መግባታቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ – (ኢ ፕ ድ)

Related Post