አርእስተ ዜና
Fri. Nov 22nd, 2024

የመንጌና የጋራንግ የመጨረሻው ስብሰባ

የመንጌና የጋራንግ የመጨረሻው ስብሰባ
የመንጌና የጋራንግ የመጨረሻው ስብሰባ

በአብይ ደምለው – ከምንወዳቸው መሪዎቻችን ለዛሬ ‘እነዚህን ብታሰባቸውስ?’ ብሎ ፌስቡክ ከትዝታ ማህደሩ መዞ ስላወጣው አብረን ብንጋራቸው አልኩ።

የደቡብ ሱዳንን ነፃ አገርነት በበላይነት የመሩትና በነፃነት ማግስትም ልዩ የክብር ቤተመንግሥት በጁባ የተሰራላቸው ፕሬዚዳንት መንግስቱ ሀይለማርያም (መንጌ)፤ በዶክተር ጆን ጋራንግ (ሌላው በሴራ የተገደሉ ምርጥ የአፍሪቃችን መሪ) እና በኩባው አብዮት መሪ ፊደል ካስትሮ መሃከል ዋናውን የግንኙነት መስመር ዘርግተዋል።
መንጌ ከሃገር ከመውጣታቸው አንድ ሳምንት ሲቀር ከ SPLM መሪው ከዶክተር ጆን ጋራንግ ጋር በነበራቸው የምስጢር ስብሰባ አገር ለቀው እንደሚሄዱ በብቸኝነት የነገሯቸው ለጋራንግ ብቻ ነበር።

“…ይህንን ሁሉ አመት ለአገሬ ዕድገትና ሉዓላዊነት ባቅሜ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ይሁንና አሁን ጦርነቱ ያለው ከወያኔና ሻዕቢያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከልዕለ-ሃያሉንም ጋር ስለሆነ እና በተለይም በራሴው ጓዶችም ጭምር እየተከዳሁ ስለሆነ የራሴን ውሳኔ ወስጃለሁ!” ይሏቸዋል።
ጆን ጋራንግ መልሰው “…መንግሥቱ አንተ እኮ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአካባቢው እንዲሁም ለመላው አፍሪቃ ታስፈልገናለህ። ባይሆን ሙሉ ደቡብ ሱዳንን ይዞ የሚዋጋውን ግዙፍ ሠራዊቴን ላምጣልህና ወያኔን ሰሜን ሸዋና አምቦ ላይ ከበን እንደምስሰው” ይሏቸዋል።

መንጌ ቀበል አድርገው “…አመሰግናለሁ ወንድሜ! አንተ ለእኔ ትልቅ ውለታ የምትውልልኝ ለአመታት የደከምንበትን የደቡብ ሱዳንን ነፃነት ስታውጅ ብቻ ነው።
“…እኔ ደክሞኛል! ሁሉን አቅሜን አሟጥጬ ጨርሻለሁ። አሁን እኮ ጦርነቱ ከውስጥም ጭምር ነው…እዚሁ ጓዳዬ ውስጥ!

“…ስለዚህ ያንተ ወታደሮች የህይወት መስዋዕትነት መክፈል ካለባቸው ለሃገራቸው ነፃነት እንጂ ለኢትዮጵያ መሆን የለበትም።” አሏቸው።

“…ባይሆን ያንተንና የ SPLM ቀጣይ መቀመጫ ኬንያ እንዲሆን ከአራፕ ሞይ ጋር ተነጋግረናል። ወያኔ በ CIA ጭምር እየተደገፈ ስለሆነ ከዚህ በኋላ ለእናንተ በኢትዮጵያ ቢሯችሁ ለመቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል።

“…ስለዚህ ዋና ቢሮህንንና ማዘዣ ማዕከልህን ወደ ናይሮቢ ማዞር አለብህ። የምትፈልገውን የአየር መጓጓዝ በሙሉ እኛ እናመቻቻለን…” አሉ መንጌ።
የሁለቱ ፍቅር እጅግ የተለየ ነበር።

ደቡብ ሱዳን ነፃ እንደወጣችም ጆን ጋራንግ፣ ያሁኑ ፕሬዚዳንት ሪያክ ማቻር እና የተቃዋሚው መሪ ጭምር ሀራሬ ዚምባቡዌ ድረስ በተደጋጋሚ ሄደው መንጌን አመስግነዋቸዋል።

በመንጌና በብዙዎች እንደተፈራውም፤ የዶክተር ጆን ጥልቅ ፓን-አፍሪቃዊ ርዕዮት ያስፈራቸው ሰሜን ሱዳን፣ ግብፅ፣ ዩጋንዳ እና CIA በፈጠሩት ቅንብር ጋራንግ በሄሊኮፕተር “አደጋ” ተገድለዋል።

ይሁንና ዛሬም ድረስ… የደቡብ ሱዳንን ፖለቲከኞች እየደወሉና ሀራሬ ድረስ ጭምር እየጠሩ ሁሉንም የሚገስፁትና የሚቆጡት ራሳቸው መንጌ ናቸው።
ደቡብ ሱዳን “Father of the Nation” (መስራች አባቶች) ብላ የክብር ማዕረግ የሰጠችው ለዶክተር ጆን ጋራንግ እና ለፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሀይለማርያም ብቻ ነው።

የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ድርጅት SPLM መቀመጫውን አዲስአበባ አድርጎ፣ የጦር ማዘዣውን፣ ማሰልጠኛ እና ማስታጠቂያውን ደግሞ ጋምቤላ ላይ አድርጎ ከ35 አመት በላይ የኖረ አንጋፋ ነፃ አውጪ ቡድን ነበር።

ደቡብ ሱዳን ውስጥ ዛሬም ድረስ መንጌ በክብር የሚወደሱ ብቻ ሳይሆን “መንጌ” በሚል ስም የሚጠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስዎች የሚኖሩባት አገር ናት።
ቸር እንዋል!!!

Related Post