አርእስተ ዜና
Mon. Jan 27th, 2025

ዓለሙ አበራ ማን ናቸው

ዓለሙ አበራ ማን ናቸው
ዓለሙ አበራ ማን ናቸው

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የንግድ ባንክ 80ኛ ዓመት በተከበረበትና ባለ53ወለሉን ህንጻ በመረቁበት ወቅት በኢኮኖሚው ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አምስት አካላትን ሸልመዋል። ከነዚህ አንዱ አቶ ዓለሙ አበራ ናቸው።

አቶ ዓለሙ አበራ
በቀድሞው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት በባሌ አውራጃ ጊኒር ከተማ ተወለዱ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊኒር መኩሪያ ተሰማ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በዘመኑ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአካባቢው ባለመኖሩ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ካዛንችስ አካባቢ በሚገኘው በቀድሞው የአስፋው ወሰን 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። በዩኒቨርሲቲውም በቢዝነስ ትምህርት ክፍል ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ ሆነው በንግድ ሥራ አመራር እና በሕግ ዲግሪያቸውን አገኙ። ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ስዊድን በመሄድም በባንኪንግ የትምህርት መስክ ተጨማሪ ዕውቀት ቀስመው ተመልሰዋል።



የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወቅቱ ከዩኒቨርሲቲ በላቀ ውጤት የሚመረቁ ተማሪዎች ለማግኘት የሥራ ዕድል ይሰጥ ስለነበር የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳሉ ባገኙት የትርፍ ሰዓት የሥራ ዕድል አማካኝነት ከባንኩ አሠራር ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ። በመስከረም 1959 ዓ.ም የባንኩ ቋሚ ሠራተኛ ሆነው በኦርጋናይዜሽን እና ሜተድስ ክፍል ውስጥ ጀማሪ የባንክ ባለሞያ ሆነው ተቀጠሩ።

እኒህ ሰው በከፍተኛ አመራርነት የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ ለማሳደግና የቅርንጫፎች ሥርጭት ለማስፋፋት ያደረጓቸው ጥረቶች የሚጠቀሱ ናቸው። በኃላፊት ዘመናቸው ባንኩ ገጥሞት የነበረውን ከፍተኛ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቋቋም የተለያዩ አማራጮችን ሥራ ላይ በማዋል አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ማድረጋቸው ይታወቃል። ከእዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ሀገር የባንክና የንግድ አገልግሎቱ በተሻለ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ሲሆኑ ለእዚህም የተለያዩ ተቋማት ለባንኩ ዕውቅና መስጠት አስችሏቸዋል።

እርሳቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዘዳንት በነበሩባቸው ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል:-

•ከደርግ መንግሥት በፊት የግል ባንኮች የነበሩት በደርግ ተወርሰው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲዋሐዱ ሲደረግ የተለያዩ የሥራ ዲሲፒሊን እና አሠራር ይዘው የመጡትን ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት አንድ በማድረግ የባንክ ሥራ እንዲቀጥል በማስቻል በኩል ከፍተኛ የመሪነት ሚና ተጫውተዋል፣

•በጣም ጥቂት የነበሩት የባንክ ቅርንጫፎች እንዲስፋፉ ጥረት አድርገዋል።

• የደርግ መንግሥት የሶሻሊስት ርእዮተ ዓለም እከተላለሁ ሲል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ባንኮች ጫና ደርሶበት፣ በጥሩ ሁኔታ ላይ የነበረው የባንኮች ግንኙነት (Correspondent Banking Relation) እንዳይበላሽ ለማድረግ ልዩ ጥበብ በመጠቀም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠንካራ የCorrespondent Banking Relation እንዲኖር ከፍተኛ ሥራ ሠርተዋል፣



• በርካታ የባንኩ ሠራተኞች እና የማኔጅመንት አባላት በዓለም አንቱ በተባሉ የንግድ ባንኮች ኢንስትቲዩሽኖች ውስጥ የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ ሣልጠና እንዲያገኙ እንዲሁም on the job training program ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል። በመሆኑም የባንኩ ማኔጅመንት እና ሠራተኞች ከዓለም አቀፍ የባንክ ሥራ ጋር እንዲለማመዱ እና ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ረድቷቸዋል።

•እንደዚሁም ኤክስፖርት እና ኢምፖርት ካለምንም እንከንና ጥርጣሬ በተቀላጠፈ መንገድ በውጭ ትላልቅ ባንኮች በኩል እንዲስተናገዱ አድርገዋል።
እኒህ ታላቅ ሰው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከነበራቸው የአገልግሎት ዘመን በመቀጠል የዳበረ የባንክ ሥራ ልምዳቸውን ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በማጋራት የመሪነት አሻራቸውን ማኖር ችለዋል፡፡

በደቡባዊ አፍሪካ የሌሴቶ ብሔራዊ ባንክ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በመሥራት ሀገሪቱ የነበረባትን የፋይናንስ ችግር ማስተካከል ችለዋል። የዩጋንዳ ንግድ ባንክ ፕሬዚደንት በነበሩበትም ወቅት ባንኩን ከገባበት ቀውስ በማውጣት ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል አስችለዋል። በታንዛንያም የብሔራዊው ባንክ ገዥ ዋና አማካሪ በመሆን ለ8 ዓመታት አገልግለዋል።

እኒህ ታላቅ የባንክ ሰው አሁንም በሥራ ላይ ናቸው። ዕረፍት የማያውቁት ብርቱ ሰው ሥራ በቃኝ አላሉም። በጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ከሚገኙት የሀገሪቱ ባንኮች አንዱ የሆነውን ቡፋሎ ንግድ ባንክ በፕሬዘዳንትነት እየመሩ ይገኛሉ።



የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራዎች በደርግ መንግሥት ወቅት እንደ ሌሎች የሶሻሊስት ሀገሮች ባንኮች ከዓለም አቀፍ ባንኮች እንዳይነጠል አድርገውታል፡፡ ከመነጠል ይልቅ የተጠናከረ ግንኙነት እንዲኖረው በማድረጋቸው ከደርግ ውድቀት በኋላ ምንም ችግር ሳይገጥመው International Banking Business እንዲቀጥል አስችለውታል፡፡

በዚህም ሀገራችን በወቅቱ ከገጠማት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንድትወጣ ከፍተኛ ድርሻ በመጫወት ለኢኮኖሚ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ
በማበርከተቸው ኮሚቴው በ80ኛ ዓመት በዓልና በዋናው መ/ቤት ሕንፃ ምረቃ ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር እጅ ልዩ ሽልማትና ዕውቅና እንዲሰጣቸው ያቀረባቸው እኒህ ታላቅ የባንክ መሪ ክቡር አቶ ዓለሙ አበራ ይባላሉ፡፡

Related Post