በኢትዮጵያ ፕሬስ ድረጅት የተፈጸመ ወንጀል

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድረጅት የተፈጸመ ወንጀል

Opinion

ባየልኝ ባይሳ – የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በ1933 ሲመሰረት በመጀመሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣን ለአንባብያን በማድረስ ሲሆን ስያሜውም ፋሺስት ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ተባራ ነጻነት ከተመለሰ በህዋላ የተፈጠረውን አዲስ ዘመን ለማብሰር ነበር፡፡

በዛን ወቅት ሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች በቅኝ አገዛዝ የሚማቅቁበት ወቅት ስለነበር በሀገሮቹ ከቅኝ ገዥዎች የፕሮፖጋንዳ ጋዜጦች በስተቀር ሌሎች ጋዜጦች አልነበሩም ፡፡ በዚህ ረገድ አዲስ ዘመን ጋዜጣ የመጀመሪያው ሀገር በቀል የአፍሪካ ጋዜጣ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ድርጅቱ በቀጣዮቹ አስርታት ኢትዮጵያን ሄራልድን ቀጥሎም አልአለምንና በሪሳ ጋዜጦችን በማሳታም ሀገሬውን ብቻ ሳይሆን አለም አቀፉን ህብረተሰብ መረጃ በማድረስ የበኩሉን ሚና ተጫውቶአል፡፡

በርግጥ ጋዜጦቹ በሶስቱም የአገዛዝ ዘመኖች የገዥዎች መሳሪያዎች ሆነው ማገልገላቸው እሙን ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም በስርአቶቹ አምባገነን አገዛዝ ሰፍኖ ስለነበር ነው፡፡በተለይ በዘውዱ አገዛዝ የማኅበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካው ደረጃው ሁዋላ ቀር በመሆኑ ፕሬሱም በዚያው ደረጃ ነበር፡፡

የደርግ አገዛዝም ከዚያ የከፋ በመሆኑ የቃለ አቀባይነቱን ስራ ቀጥሎበታል፡፡ከ1983 እስከ 1997 በሀገሪቱ አንጻራዊ የሚድያ ምህዳር ገርበብ ተብሎ ተከፍቶ የነበር ቢሆንም ከዚያ በህዋላ ግን ወደ ነበረበት ተመልሶአል፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን ባለፉት 70 አመታት የኢት ፐሬስ የኢትዮጵያን ዘመናዊ የኢትዮጵያን ታሪክ ዘግቦ በማስቀመጥ ታሪካዊ ሚናውን ተጫውተል፡፡ ዛሬ እንደእነ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች በስራዎቻቸው ላይ ብዙውን ጊዜ አዲስ ዘመንና ሄራልድን በዋቢት መጥቀሳቸው ለዚህ አመልካች ነው፡፡

ለስነ ጽኁፍ እድገትም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን የሀገሪቱ ብርቅየ ደራስያንና ጸኀፍት ጋሽ ጳውሎስ ኞኞ፤በአሉ ግርማና ሙሉጌታ ሉሌ የዚህ ድርጅት የበኩር ልጆች ናቸው፡፡ ከ1983 በህዋላ የግሉ ፕሬስ በአበበት ወቅት አበዛኛዎቹ ጋዜጠኞ ከዚሁ ድርጅት የተገኙ እንደነበር ማንም አይዘነጋውም፡፡

ይህን የመሰለ መሰረት ያለው ድርጅት ባለፉት 15 አመታት ውስጥ የውድቀት ጉዞውን ለመቀጠል የተገደደበት ምክንያት መሪ ተብለው የተቀመጡት ሰዎች ከሙያው ይልቅ የፖለቲካ ታማኝነታቸው ያዘነበለና ለሙያወ ክብር ያልሰጡ ስለነበር ነው፡፡የተባሉትን ከመፈጸም በስተቀር ስለ ስራቸውም ሆነ ስለ ሰራተኛው መብት እምብዛም አይጨነቁም ነበር፡፡

በስተመጨረሻም ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ ባለፈው አመት በደ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ቡድን ከከፍተኛ የህዝብ መስዋእትነትበህዋላ ወደ ስልጣን በመውጣቱ ለሀገሪቱም ሆነ ለሚዲያው ትልቅ ተስፋ ሊፈነጥቅ ችሎአል፡፡

እንደ ሌሎች መስሪያቤቶች የኢትዮጵያ ፕሬስ ድረጅትየለውጡ ንፋስ ደርሶ ዋናውና ምክትል ስራ አስኪያጆች ለቦታው አይመጥኑም ተብለው ከስራቸው ተባረዋል፡፡ ይህም ለድርጅቱ ታላቅ እፎይታን አስፎኖአል፡፡ምን ያደርጋል ግን እነሱ ከግብረአበሮቻቸው ጋር የፈጸሙት ወንጀልና ትተው የሄዱት ሰንኮፍ ተቁዋሙን እያሽመደመደ ይገኛል፡፡

ይህ የተፈጸመው ወንጀል እንዲህ ነው፡፡ በ2010 አም በድረጅቱ አዲስ መዋቅርና የሰራተኞች ድልድል እናካሂዳለን በሚል የመደልደያ ማኑዋል አዘጋጁ፡፡

ይህን ማኑዋል ግን የነበረው የአመራር ቦርድ አያውቀውም ነገር ግን በዚያ ህገ ወጥ መንገድ ድልደሉን በማካሄድ የሚፈልጉዋቸውን የጥፋታቸው ተባባሪዎችን ለዚያውም በህገ ወጥ መንገድ የተቀጠሩትን እስከ አራት ደረጃ አሳድገው ተቀኛቃኜ ናቸው፤የተለየ አመለካከት አላቸው የሚሉዋቸውን ሰራተኞች ግን እሰከ ሶስት ደረጃ ዝቅ አድርገው ተበቅለዋቸዋል፡፡

በዚህ ሳቢያም ወደ 24 ሰራተኞች ቅሬታ አቅርበው ጉዳዩን እስከ ፍርድ ቤት አድርሰውታል፡፡ ሌሎች ቅሬታ ያደረባቸው ሰራተኞች ደግሞ ብከስ ምን አመጣለሁ በማለትና በፍትህ አካላቱ ላይ ተስፋ በማጣት ቅሬታቸውን በሆዳቸው ይዘው ማስታመምን መረጡ፡፡

ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዘው የሄዱት ጉዳያቸው ከመጀመሪያወ ፍርድ ቤት አልፎ ወደ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ሲቀርብ እያታየ የመደልደያ ማኑዋል እንዲታይ ይቅረብ ተብሎ ፍርድ ቤት ያዛል፡፡

ነገር ግን በቀድሞዎቹ ዋና እና ምክትል ስራ አስኪያጆች የሚመረው ቡድን በማፍያዊ አካሄድ ትክክለኛውን ማኑዋል ማቅረብ ትቶ ፎረጅድ የሆነና የተለየ ፊርማ ያለው ማኑዋል አቅርቦ ጉዳዩን ለጊዜው ለማዳፈን ሞክሮአል፡፡ ይህን ማረጋገጥ የሚፈልግ ዋናውንና ቅጅውን ማመሳከር ይችላል ዶክመንቱም በግለሰቦች እጅ ይገኛል፡፡

በመቀጠልም ይህ ጉዳይ እንዴት ሊሆን ቻለ ተብሎ መዝገብ ቤት ያለው ፋይል ይጣራ ሲባል የተፈጸመው ወንጀል መሆኑ እየታወቀና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተመርቶ እንዲመረመር ማድረግ ሲገባው አመራሩ ለርሱ ታማኝ የሆኑ አሽከሮችን ኮሚቴ ብሎ አዋቅሮ ጉዳዩ እንዲመረመር በማድረግ የተከሰሱት የመዝገብ ቤት ሰራተኞች በነጻ እንዲሰናበቱ አድርገል፡፡

ይህ የሌብነት አካሄድ የፈለገውን ያህል ጊዜ ቢራዘምም ወንጀለኞቹ ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ የመጣው በወጣት የተሞላው አመራር በመስሪያ ቤቱ ያለውን የተከማቸ በደልና ኢፍትሀዊ አሰራር ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡

ከላይ የተፈጸመውን ማፍያዊ ድርጊተም በተገቢው ያውቃል ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ትንፍሽ አለማለቱ በጥርጣሬ እነዲታይ እያደረገው ሲሆን ቅቡልነቱም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈበት ይገኛል፡፡ነገር ግን መዘዙ ሌላ ጣጣ ሊያመጣ እንደሚችል ይገነዘባል ተብሎ ይታመናል፡፡
አሁን አመራሩን የከበቡት በህገ ወጥ መንገድ የተቀጠሩ ሰዎች

የውጭ ቋንቋ፤የሀገር ውሰጥቁዋንቐ ዲፓርትመንቶች ሀላፊዎች፤የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፤ ሶስት ሙያተኞች ከጥናትና ምርምር ዲፓርትሜንት፤አንድ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ የቡድን አስተባባሪ እና ሌሎችም አመጣጣቸው በሙስና ነው፡፡የብዙ ዜጎችን የመወዳደር እድልና የውስጥ እድገትን አምክኖአል፡፡

ሙስና ደግሞ በደ/ር አብይ አገላለጽና በእኛም ጭምር ሌብነት ነው፡፡ሌብነት ወንጀልና የሚያስጠይቅ እኩይ ተግባር ነው፡፡ መንግስት ሙስናን የማይሸከም ትውልድ እፈጥራለሁ እያለ በአንድ ተቁዋም ሌቦች በአመራር ቦታ እንዲቀጥሉ መተባበር የሚስጠይቅ ድርጊት ነው፡፡

“አሁን የበልቼ ልሙት” ፖለተካ አከርካሪውን ተመቶ ወደ ጥግ ቢገፋም በሀገራችን እየተካሄዱ ያሉትን ብጥብጦች ከጀርባ በገንዘብ እንደሚደግፍ ይታወቃል፡፡ ስለሆነም ለሁላችንም ሰለም የሚበጀን ወንጀለኞችን ማጋለጥ ግዴታ ነው፡፡

ይህ መስሪ ቤት በቦርድ የሚመራ ነው፡፡ የቦርዱ ሊቀመንበር አቶ ካሳሁን ጎፌ የኦዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ይህ ማለት ከመንግስት የሀላፊነት ቦታቸው በተጨማሪ የፓርቲም ሀላፊነት አለባቸው፡፡ፓርቲያቸው ሀገራችን አሁን ለተጎነጸፈችው የነጻነት ብርሀን ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተ ነው፡፡

ያ ሁሉ መስዋእትነት የተከፈለውም ለእውነተኛ አላማ እንጂ አርጌውንና የዘረፋ ፖለቲካ ለማስቀጠል አይደለም፡፡ ጥፋቶችን እንዳላዩ ማለፍ የተከፈለውን መስዋእትነት መዘንጋት ይሆናል፡፡ ይህ ተቁዋምም በደሀው የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ሀገር ለማገልገል እንጂ ጊዜ ወለድ ማፍየዎችን ለመቀለብ የተመሰረተ አይደለም፡፡

ስለሆነም ሳይረፍድ መፍትሄ ማፈላለጉ ለአዲሱ አመራር የሚበጅ ነው፡፡ የተጠቀሱት ሰዎች በአመራር ውስጥ መቀጠላቸው በአዲሱ አመራር ቁመናን ያጠለሻል ፡፡ ከሰሞኑ በአዲሱ አመራር የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎችም ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ ስለሆነም ጊዜ ሳይረፍድ ለተገለጸው ችግር መፍትሄ ይሰጠው፡፡