መንግስት ዛሬም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ትኩረት ይስጥ

መንግስት ዛሬም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ትኩረት ይስጥ

Opinion

በኢትዮጵያ በዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ሀገራችን እጅግ አስደሳች የሆነ የለውጥ ርምጃ እየታየ ሲሆን የወደፊቱም የሀገራችን ተስፋ ብሩህ መሆኑን አመላክቶአል፡፡ ለውጡን ተከትሎም በተለይ ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል በመንግስት ተቁዋማት ውስጥ ያለ አንዳች ብቃት በአመራር ላይ ተቀምጠው የሀገሪቱን ተስፋ ሲያጨልሙ የነበሩ ደካሞችን በማንሳት በተገቢውና ብቃት ባላቸው ሰዎች መተካት ነው፡፡ ይህም መበረታታት የሚገባው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም የለውጡ ትሩፋት ደርሶት ድርጅቱን ከሁለት አስርታት በላይ በዳዴ ሲያስካሂድ የነበረው ስራ አስኪያጅ ከእነ ምክትሉ ከቦታው እንዲነሳ መደረጉ ትልቅ ተስፋ አምጥቶ ነበር፡፡ በተመሳሳይም በወ/ሮ ፍሬህይወት አያሌው የሚመራው ቦርድ ከቦታው ተነስቶ በአዲስ የቦርደ አመራር እንዲተካ መደረጉም ትልቅ ተስፋን አጭሮ ነበር፡፡

ነገር ግን የተደረገው ተስፋ ጉም መዝገን ሆኖ በአቶ ካሳሁን ጎፌ የተመራው አዲሱ የድርጅቱ ቦርድ ስራ እንደጀመረ የድሮውን አገዛዝ ለማስቀጠል የቆረጠ መሆኑን በይፋ አሳውቆአል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ከሰራተኛው ጋር ስብሰባ ሲቀመጥ በፊት በነበረው አመራር የተፈጠሩ ግድፈቶች እንደማይታረሙ ሰራተኞችም በደላቸውን ውጠው አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በተለይ ቀደም ሲል በድርጅቱ አመራር በህገ ወጥ ሰነድ ድልድል ተፈጽሞ በደልየደረሰባቸው ሰራተኞች ብትፈልጉ ክሰሱ የተፈጠረው ስህተት አይታረምም ብሎ በይፋ ተናግሮአል፡፡

ይህ ብቻ ሳያንስ የተፈለገውን ያህል ብትደክሙም ጋዜጣችሁ አንባቢ የለውም በሚል ፍርደገምድላዊ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይህም ብዙዎችን አሳዝኖአል ነገር ግን እንዲህ ሊሉ የቻሉት የሰራ መሰረታቸው ከሚዲያ ባለመሆኑ የተነሳ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

አቶ ካሳሁን ጎፌ በኢትዮጵያ ጵሬስ ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲሾሙ ዛሬ የድርጅቱ ዋና እና ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሰሩ ያሾሟቸው ከእርሳቸው ጋር ባላቸው ግላዊ ቅርርበት እንጂ የሰራ መሰረታቸው ከህትመት ሚዲያ ሆኖ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ምን ያህል ለስራው ትኩረት እንዳልተሰጠ በግልጽ ያመለክታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ የፐብሊክ ሚዲያው አሁንም ደካማ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጹታል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን የሚመለከተውና ለቦታው ብቁ የሆነ ሰው እስካልተመደበ ድረስ ችግሩ ተባብሶ እንደሚቀጥል ምንም ጥርጥር አይኑረን፡፡

ዛሬ በህዝብ ተወዳጅነታቸው የሚታወቁት እንደ ሸገርና ሬድዮ ፋና ያሉት ሚዲያዎች ለዚህ የበቁት በአመራራቸው ጠንካራነት እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ የኢት ጵሬስ ድርጅት ዛሬም የውስጥ ችግሩን ይዞ ሰራተኛው ብሶቱን በውስጡ ይዞ እየቆዘመ ስራውን የእንጀራ ጉዳይ ብቻ አድርጎት እየሰራ ይገኛል፡፡ አሁን ያለው አመራርም የድሮውን አሮጌ አሰራር ለማስቀተል ሌት ተቀን እየተጋ ይገኛል፡፡ ወጣት ጋዜጠኞችም እንዲሁ ከአቅማቸው በታች በፍርሀት ተሸብበው ይሰራሉ፡፡

ከምክትል ስራ አስኪያጅ በታች ያሉ የስራ ሀላፊዎች ለምሳሌ የፕሮዳክሽን ክፍል ኀላፊ የቋንቋ ምሩቅ ሆኖ የዲዛይን፤የልዩዩ ክፍል፤የኦን ላይን ክፍል ሀላፊ እንዲሆን የተመደበው ሳይወዳደር ለቀድሞው ምክትል ስራ አስኪያጅ በነበረው ቅርበት የኦን ላይን ሚዲያውን በህወሀት ፍላጎት ለማስኬድ ነበር፡፡ አሁንም ይህ ሁኔታ ቀጥሎአል፡፡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቁዋንቁዎች ክፍል ሀላፊዎች ያለ ውድድር የተቀጠሩ ሲሆን በቦታቸው ላይ ቀጥለዋል፡፡

የገበያ ልማት ክፍል ሀላፊ ሆና ግልጽ ባለ ሁኔታ መቀጠርዋ ሳያንስ ለእርስዋ የተመደበውን የድርጅቱን መኪና ባለቤትዋ ጠዋት ከቤትዋ አምጥቶ ቀኑን ሙሉ ሲጠቀምበት ውሎ ማታ አስራ አንድ ሰአት ላይ መኪናውን ይዞ መጥቶ ወደ ቤታቸው ይዞአት ይሄዳል፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያሳየው የድርጅቱን መኪና የመስራያ ቤቱ ባልደረባ የሆነ ሰው በድርጅቱ ነዳጅ አላግባብ እየተጫወተበት የሚገኝ መሆኑን ሲሆን መኪናው አደጋ ቢያደርስ ኢንሸራንስ በማን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ይህንን ሁኔታ ሀላፊዎች ወይም የድርጅቱ የክዋኔ ኦዲተርዋ አላየሁም አልሰማሁም ብለው ዝም ብለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ነገ ሊያስጠይቅ እንደሚችል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ከሰሞኑ የኢትየጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ካሳሁን ጎፌ ከነበሩበት ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታነት ተቀይረው ወደ ኦሮምያ ክልል ግብርና ቢሮ ተዛውረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታም በቦርድ አመራርነት ስለማይቀጥሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እጅግ መልካም አጋጣሚ ተፈጠሮለታል፡፡ ስለሆነም ለስራው የሚመጥንና ለሙያው ታማኝ የቦርድ ሰብሳቢ ይህን ተከትሎም አዲስ ብቃት ያለው የተቁዋም አመራር እንዲመጣ መንግስት አፋጣኝ የመፍትሄ ርምጃ ይውሰድ፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያም የሚሰሩትን በሚያውቁ ሰዎች በመመራት ሀላፊነቱን በተገቢው ይወጣ፡፡