የወጪ ንግድ ገቢ በ95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጨመረ

የወጪ ንግድ ገቢ በ95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጨመረ

News

የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የሦስት ወራት የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወራት ጋር ሲነጻጸር በ95.01 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም 15.13%ገቢ መጨመሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት 797.78 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈፃፀም የተመዘገበው 723.04 ሚሊዮን ወይም 90.63% የአሜሪካን ዶላር መሆኑን በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በመጀመሪያ ሩብ ዓመት በውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደቅደም ተከተላቸው ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን፣ የብርዕና አገዳ እህሎች፣ አበባ፣ ኤሌክትሪክ እና ጫት ናቸው ፡፡

እንዲሁም የዕቅዳቸውን ከ75% እስከ 99% ክንውን ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ደግሞ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቡና፣ የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት እና አትክልትና ፍራፍሬ ሲሆኑ፤ የቅባት እህሎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ባህር ዛፍ፣ የቁም እንስሳት፣ ሰም፣ ስጋ፣ ታንታለም፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና ወተትና የወተት ተዋፅኦ የእቅዳቸውን ከ50% እስከ 74% ክንውን አስመዝግበዋል፡፡

በሌላ በኩል ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ሻይ ቅጠል፣ ምግብ መጠጥና ፋርማስዩቲካልስ፣ ቅመማ ቅመም፣ ሌሎች ማዕድናት፣ ወርቅ፣ የስጋ ተረፈ ምርት፣ ማር፣ ብረታ ብረት እና አሳ ናቸው፡፡

የወጪ ንግድ አፈጻጸም ለመጨመሩ የኢኪኖሚ ሪፎርሙ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በዚህ መሰረት በወጪ ንግድ የተሰማሩ የዘርፉ ተዋናዋዮች በቅንጅት እና በጋራ ከተቋሙ ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ መደረጉ ፤ ላኪዎች ከዓለም የገበያ ዋጋ ምርትን አሳንሶ መሸጥ የሚያስጠይቅ እንደሆነና የወጪ ንግድ ኮንትራት አስተዳደር ለመምራት በወጣው መመሪያ ላይ ለላኪዎች ግንዛቤ መፈጠሩ ለወጪ ንግድ አፈጻጸም መሻሻል አስተጽኦ ማበርከቱ ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም የወጪ ንግዱ ከዚህ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው የሚላኩትን የግብርና ምርቶችን መጠን መጨመር ፣ በጥራት ለገበያ ማቅረብ እና ለገበያ ያልቀረበውን የምርት ክምችት አሟጦ እንዲወጣ በማድረግ እና በቅንጅት መስራት፤ የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል ለድርጅቶች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣ የሚስተዋሉባቸውን ውስጣዊም ሆነ ውጪያዊ ችግሮች መፍታት እና ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ፤ የማዕድን ዘርፉንም ወደ ስራ ያልገቡትን ኩባንያዎች ፈጥነው ስራ እንዲጀምሩ ማድረግ፤ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት ከዚህ በፊት በየደረጃው በአሠራር፣ በአደረጃጀት፣ በአቅርቦትና በክህሎት ዙሪያ የተለዩትን ክፍተቶች መቅረፍ፤ በተለይም የወጪ ንግድ ቁልፍ ችግር የሆነውን የኮንትሮባንድ ንግድ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመከላከል የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር መስራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በአጠቃላይ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት እና የወጪ ንግዱን ከዚህ በበለጠ ለማሻሻል የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን በተቀናጀ አግባብ በተሟላ ሁኔታ ተጠናክሮ በመስራት፤ ከአምራቾች፣ ከአቅራቢዎችና ከላኪዎች ጋር ተቀናጅቶ በመተግበር የወጪ ንግዱን ገቢ ማሻሻል እንደሚገባ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡