የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ እሁድ ይመረቃል

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ እሁድ ይመረቃል

News

የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑ በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ እሁድ በይፋ እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገነቡት አራት ስኳር ፋብሪካዎች አንዱ ነው፡፡

ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቀን ከ8 ሺህ አስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን ጥሬ ስኳር፣ ነጭ ስኳር እና የተጣራ ስኳር ያመርታል ተብሏል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ መመረቅ ስኳር የሚያመርቱት ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ ስምንት ያደርሰዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የግንባታ ሥራው በይፋ የተጀመረው በመጋቢት ወር 2008 ዓመተ ምህረት ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ነው፡፡

ለአራቱም ስኳር ፋብሪካዎች የሚውል በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ለማልማት በኦሞ ወንዝ ላይ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጥቅሉ 30 ሺህ ሄክታር መሬት ውሃ ገብ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉን ከስኳር ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እስከ አሁን በቋሚ፣ በኮንትራትና ጊዜያዊነት ከ110 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከ300 በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ከመጋቢት 2009 ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡

(በኤፍ.ቢ.ሲ)