ባቱ በዝዋይ ሐይቅ ዙሪያ ሆቴል እንዲከፍቱ ባለ ሃብቶችን ጋበዘች

News

ከአዲስ አበባ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ በ160 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኘዋ የባቱ (ዝዋይ) ከተማ ባማረዉ የዝዋይ ሀይቅ ዙሪያ 17.1 (17000 ካሬ ሜ.) ቦታ ላይ ሆቴል እና ሎጅ መገንባት ለሚፈልጉ ባለ ሀብቶች ያዘጋጀሁ ስለሆነ መጥታችሁ ኢንቨስት አድርጉ በማለት ጥሪ አቅርባለች፡፡

የባቱ ከተማ ም/ ከንቲባ አቶ ነቢ ጉደታ ለበሐቅ መልቲ ሚዲያ እንደ ገለፁት ከሆነ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ ሀይሌ ሪዞርት ዓይነት የእንግዳ ማረፊያዎች በሐይቁ ዙሪያ በመከፈታቸዉ ከተማዋን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር በመጨመር ላይ ነዉ፡፡

በዝዋይ ሀይቅ ላይ የሚገኙ ሰዎች የሚኖሩባቸዉ አምስት ደሴቶች ከፍተኛ የቱሪስት መስህቦች እንደሆኑ የተናገሩት ም/ ከንቲባ ነቢ፣ በሆቴል እና በማስጎብኘት ስራ የተሰማሩ የሃገር ዉስጥ እና የዉጭ ባለ ሃብቶች በከተማዋ መዋዕለ-ነዋያቸዉን ቢያፈሱ ዉጤታማ እንደሚሆኑ ተናግዋል፡፡

ነገር ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ መሬት ወስደዉ እና አደልበዉ ለሶስተኛ ወገን ለማዞር የሚያስቡ አጭበርባሪ ባለ ሀብቶችን የከተማዉ አስተዳደር እንደማይታገስ እና መሬቱን ወስደዉ በቶሎ ወደ ስራ መግባት ለሚፈልጉ እዉነተኛ ባለሃብቶች የሚሰጥ መሆኑን አቶ ነቢ ገልፀዋል፡፡

በቅርብ ጊዜም ከ 10 ዓመት በላይ በሐይቁ ዙሪያ መሬት ይዘዉ ወደ ስራ ካልገቡ ባለለሃብቶች ብዙ ሄክታር መሬት የከተማዉ አስተዳደር እንደ ነጠቀ አቶ ነቢ ይናገራሉ፡፡