18 ተጠርጣሪዎች ከህገ ወጥ ገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ዋሉ

18 ተጠርጣሪዎች ከህገ ወጥ ገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ዋሉ

Amharic

ከህገ ወጥ ገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች 18 መድረሳቸው ተገልጿል። የህገ-ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል እየተካሄደ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።

ባለፉት ቀናት በተከናወነ ኦፕሬሽን 10 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ፣ ከ1 ሺህ በላይ የነብስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች፣ ሁለት መትረየሶችና 80 ሺህ የክላሽ እና የሽጉጥ ጥይቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና 570 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በህገ-ወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ጅግጅጋ ሲጓጓዝ በቁጥጥር ስር መዋሉን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሽፈራው ጉቱ ፥ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረው ይህ ዶላር ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማ መሰረት ሎሜ ወረዳ የፍጥነት መንገድ መውጫ ላይ በቁጥጥር ስር እንደዋለ ነው የተነገረው።

ቶዮታ ሃይሉክስ መኪና የፍጥነት መንገድ መውጫ ላይ ዛሬ 7 ሰዓት አካባቢ ለክፍያ ሲቆም በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ገንዘቡ መገኘቱን ኮማንደር ሽፈራው ጉቱ ገልፀዋል።

ለጊዜው የወንጀሉ ተጠርጣሪ አንድ ግለሰብ ከተሽከርካሪውና ከገንዘቡ ጋር በቁጥጥር ስር እንደዋሉና ህብረተሰቡ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን የማጋለጥ ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተያያዘ ዜና በዲላ ከተማ ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በስምንት አይሱዙ የጭነት ተሸከርካሪዎች ተጭነው ሲጓጓዙ ህብረተሰቡ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ኤዚአ ዘግቧል፡፡

(በኤፍ.ቢ.ሲ)