Site icon ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ

የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች የወለጋዉን የጅምላ ግድያ አወገዙ

የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች የወለጋዉን የጅምላ ግድያ አወገዙ

የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች የወለጋዉን የጅምላ ግድያ አወገዙ

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ምክር ቤት በምዕራብ ኢትዮጵያ በዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈጸመውን ግድያ እና ጥቃት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ገለጸ።

ኢትዮጵያ ሀገራችንን በዓለም ላይ ለአብነት ስሟ ከፍ ብሎ እንዲነገር ካደረጉት ጉዳዮች መካካል የአብሮ መኖር እሴታችን በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው። ለዓመታት የዘር፣ የቋንቋ እና የሐይማኖት ልዩነቶች ሰባራ ምክንያት ሳይሆኑን በአብሮነት ስሜት በጋራ ዘልቀናል። ይህ ላንለያይ የተጋመድንበት፣ ዘመን ያልበጠሰው ኢትዮጵያዊ ገመድ ዛሬም በአንድነት ለመኖራችን ትልቁ ምክንያት ነው።

አሁን አሁን ግን ይህን የማንነታችንን መገለጫ የሆነውን ልዩ ኢትዮጵያዊ የፍቅር ቋጠሮ በጥሶ ለመጣል በተለያየ አቅጣጫ ፈተናዎች እየተጋረጡብን ነው። ወርቅ በእሳት ይፈተናል እንዲሉ የኛም ጠንካራነት፤ ወንድማማችነት እና አንድነት በነዚህ መልካቸውን እየቀያየሩ በሚከሰቱ ፈተናዎች ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጠዋል።

ዛሬም ግን ፈተናውን ልክ እንደ ሁሌውም በብልሃት እና በቆራጥነት ተጋፍጠን ድል ለመንሳት በጋራ እና በጥንቃቄ መስራት ይጠበቅብናል። ሥራው ደግሞ የሁላችንም ነው። ወገንተኝነታችን ለህዝባችን ብቻ መሆን ይገባዋል። ከዚህ በተቃረነ ሁኔታ ዘር፣ ሐይማኖት፣ ቋንቋ እና የፖለቲካ አመለካከት ምክንያት ሆኖን አጋርነታችን የኛ ብለን ለተቀበልነው ቡድን ብቻ ከሆነ በርግጥም የዕይታ ማዕዘናችን መስመሩን ስቷል፤ ሰውን በማንነቱ ብቻ እንደ ጠላት መመልከት በየትኛውም መለኪያ ሚዛን አይደፋምና። በእርግጥም ይህ አይነቱ አተያይ ዓይንንም ልብንም የሚጋርድ፣ ለምንፈጽመው ክፉ ድርጊት ምክንያት የማይሻ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ነው ማለት ይቻላል። ሰሞኑን በምዕራብ ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያ እና በጋምቤላ ክልሎች የተከሰተው ይህ ነው።

በተለይ የሽብር ጥቃት ነው ብሎ መንግስት በገለጸው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃን ዜጎች፣ ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ በግፍ ተገድለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ንብረታቸውም ወድሟል።

ይህ ማንነትን መሰረት በማድረግ በየጊዜው በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸመ የሚገኘው ጭካኔ የተሞላበት የሰዎች ግድያ፤ ፍጅት እና ዜጎችን ከቀዬአቸው የማፈናቀል ተግባር ከሚያደርሰው አካለዊ ጉዳት ባሻገር የሚያስከትለው የስሥነ-ልቦና ጫናም ከፍተኛ ነው። ድርጊቱ እየረገበ ይሄዳል የሚል ዕምነት በብዙ ሰው ዘንድ ቢኖርም ተዳፍኖ ቆይቶ ድንገት መንደድ እንደጀመረ እሳት ዜጎችን መፍጀቱን አሁንም ቀጥሎበታል።

ድንገት እየተከሰተ የሰው ሕይወት የሚቀጥፈው እና ለነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት በመሆን ላይ የሚገኘው ይህን መሰሉ የሽብር ጥቃት በህዝብ ዘንድ የደህንነት ስጋት ከመፍጠሩም በላይ አብሮ የመኖራችንን ደግ ባህል እያጠፋብን ይገኛል።

ሰሞኑን በሀገራችን በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች የተከሰተውን እና ቁጥራቸው በውል ላልታወቀ ብዙ ንጹሃን ዜጎች መሞት፣ አካል መጉደል እና መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ዘግናኝ ጥቃት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አጥብቆ ያወግዛል።

መንግስትም፣ መሰል ሁኔታዎች ሊያስከሰቱ የሚችሉትን አጋጣሚዎች ሁሉ በማጥናት ጥቃቶቹ ከመፈጸማቸው በፊት ሊደረግ የሚገባውን የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት የማረጋገጥ ግዴታውን እንዲወጣ እያሳሰብን ከጥቃቱ በኋላ የተወሰደውን አፀፋዊ እርምጃ ይፋ እንዲያደርግም እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ምክር ቤት ያለ አግባብ በግፍ ለተገደሉ፣ አካላቸው ለጎደለ እና ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ንፁሃን ዜጎች በተለይ በህጻናት እና በሴቶች ላይ ስለደረሰው ዘግናኝ ግድያ የተሰማውን ልባዊ ሃዘን ይገልጻል። ምክር ቤታችን በዚህ አስከፊ ድርጊት ምክንያት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ መፅናናትን እንዲሁም አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ማገገመን ይመኛል።

Exit mobile version