ከህዳር 12 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ሲካሄድ የነበረው የሁዋዌ ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር አለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ)ና የዲጂታል ተሰጥኦ ልማት ስልጠና ፕሮግራም ከ12 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉ 66 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ለአንድ ሳምንት በተካሄደው ስልጠና የተሳተፉ ተማሪዎች ስለ ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ እንዲሁም እንደ 5G፣ IoT፣ Network፣ Cloud፣ የፕሮጀክት አስተዳደርና የአመራር ክህሎት በዘርፉ ልምድና እውቀት ካላቸው የአይሲቲ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎች የቀሰሙ ሲሆን የተለያዩ አገራት ባህል ልውውጥም አካሂደዋል። እ.ኤ.አ. በ2008 ሁዋዌ በዓለም ዙሪያ ባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ያሉ አገር በቀል የዲጂታል ተሰጥኦዎችን ለማልማት የሚረዳ “Seeds for the Future” የተሰኘ ፕሮግራምን አስተዋውቋል። እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ከ200 በላይ ተማሪዎችም ተሳትፈውበታል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ቼን ሚንግሊንግ በኦንላይን ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ይህ በአይሲቲ ውስጥ ያላችሁን ተሰጥኦ ለማዳበር እና የወደፊት አኗኗራችሁን የሚደግፍ እውቀት ለመቅሰም ጥሩ አጋጣሚ ነው። ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለች ሀገር እንደመሆኗ እንደ እናንተ ያለ በአይሲቲ እውቀቱ የበልጸገ ወጣት ያስፈልጋታል። እናንተ የነገ ተስፋዎች ናችሁ፡፡ ሁዋዌም እንደ እናንተ ላሉ ትውልዶች የተሻለ ነገ የሚሰጥ እና ሙሉ በሙሉ የተገናኘ፣ ኢንተሊጀንት ዓለም ለመፍጠር አልሞ የሚሰራ ድርጅት ነው።” ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ዘላለም አሰፋ በትምህርት ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ትምህርት ዋና ስራ አስፈፃሚ ገለጻ ሁዋዌ እና ትምህርት ሚኒስቴር በሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ፕሮግራም ላይ ከጅምሩ አንስቶ በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ፕሮግራሙ ለተሳታፊ ተማሪዎች ከታዋዊ የአለም አቅፍ የአይሲቲ ባለሙያዎች ጋር በማግኘት በአይሲቲ ዘርፍ ውስጥ የሚፈጠሩ አዳዲስ ለውጦችን ለማሳወቅ እድል ይፈጥራል ብለዋል። “እንደ ትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተማሪዎች እና ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ የክህሎት ማበልጸጊያ ፕሮግራም ላይ እንድትሳትፉ እንፈልጋለን” ያሉት ዶ/ር ዘላለም በዚህ ፕሮግራም ለተሳተፉት ተማሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ሁዋዌ የወጣት ተማሪዎችን ተሰጥኦዎ ለማውጣትና ለማበልጥጸግ የሚያድርገውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሚስተር ሊሚንግ ዬ በበኩላቸው “ሀገራችን ኢትዮጵያ በዲጂታል አብዮት ውስጥ እየገባች ያለች በመሆኑ በዚህ ስልጠና የቀሰማችሁት ክህሎትና እውቀት ከፍተኛ አስተዋጻኦ ያበረክታል” ብለዋል።
“እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ወጣት መሆን ስጦታ ሲሆን የቴክኖሎጂ ባለሙያ መሆንና በቴክኖሎጂ ውስጥ መሥራት ደግሞ ትልቅ እሴት ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ መሳተፍና አለም አቀፍ ልምድ መቀሰም ደግሞ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ እድገት ትልቅ እድል ነው” ሲሉ የሀሁ ጆብስ እና የምናብ አይሲቲ ሶሉሽንስ ፒኤልሲ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ቃለአብ መዝገቡ በመዝጊያው ላይ ተናግረዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት በየአመቱ አሥር ተማሪዎች በቻይና በሚገኘው የሁዋዌ ዋና መሥሪያ ቤት በአካል በመገኘት የሁለት ሳምንት ሥልጠና ሲወስዱ የቆዩ ሲሆን ከወረርሽኙ መከሰት በኃላ እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ በኦንላይን መካሄድ ቀጥሏል። ሚስተር ሊሚንግ ዬ ሁኔታውን ሲገልጹ “በኦንላይን መካሄድ መጀመሩ የተሳታፊ ተማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ አስችሏል” ብለዋል። በዘንድሮው መርሃ ግብር 69 ተማሪዎች ፈተናውን አጠናቀው ያለፉ ሲሆን 17 ተማሪዎች በሁሉም ኮርሶች መቶ መቶ ያመጡ ናቸው። የአንድ ሳምንት የኦንላይን ስልጠና ፕሮግራም የኦንላይን ትምህርቶችና እና እንዳ ባህል ልውውጥ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ መስተጋብሮች ተካሂደውበታል፡፡ ተማሪዎች በቀን ከስምንት ሰአታት በላይ በኦንላይን ትምህርትና ጥናት ላይ ያሳለፉ ሲሆን በቡድን በመሆን የሰሯቸውንም ፕሮጀክቶች ለአለም አቀፍ አማካሪዎች አቅርበው አስተያየቶችን ተቀብለዋል።
በስልጠናው፣ በባህል ልውውጥ እና በፕሮጀክት ውድድሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ከኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ቬትናም እና ሞንጎሊያ ጋር ተመድበው ተሳትፈዋል። 25 አባላት ያሏቸው ሶስት የኢትዮጵያ ቡድኖች ወደ ቀጣይ ደረጃ ያለፉ ሲሆን ሶስት ተማሪዎች ምርጥ የቡድን መሪ ተብለው እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ቡድኖቹ ቀጣይነት ያለው የምክር አገልግሎት (mentorship) ለማግኘት እና ለቀጣይ ውድድር እድል አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ አንድ “V-LASS” የተባለ ፕሮጀክት ምርጥ ፕሮጀክት ሆኖ ተመርጧል። ፕሮጀክቱ በዋነኛነት የሚያተኩረው ዓይነ ስውራንን በእይታ በማገዝ ላይ ሲሆን ዓላማውም ነጩን ዱላ በ “እይታ መነጽር” የመቀየር ነው።
ሁዋዌ ኢትዮጵያ ለስልጠናው ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እንዲሳተፉ የጋበዘ ሲሆን 12 ዩኒቨርስቲዎች 200 ተማሪዎችን መዝገበው ልከዋል፡፡ ከተደረገ ማጣሪያ በኃላም 77 የሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚ ሰልጣኞች የሆኑና የትምህርት ውጤታቸውም ከፍተኛ የሆኑት ተመርጠው ተሳትፈዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ተማሪ ፌቨን ይፍሩ “ስራ ፈጣሪዎች እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ብዙ አስተምረውኛል፣ ስለ አይሲቲ ፕሮጄክቶች ስለፕሮጀክት አስተዳደርና እቅድ ማውጣትም እውቀት አግኝቻለሁ” ስትል ተናግራለች።
ሳምሶን ብርሃኑ ሌላኛው ተሳታፊ ሲሆን “ስለአመራርነት በተማርኩት በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ወደፊት መሪ መሆን ስለምፈልግ, መሪ ለመሆን ምን እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ያገኘሁበት በጣም ጥሩ ተሞክሮ ነበር። ከቡድን አጋሮቼ ጋር በተሳተፍኩበት ፕሮጀክትም ብዙ ተምሬያሁ፣ አለም በ2050 በዲጂታል ቴክኖሎጂ የት እንድምትደርስ በመገንዘብ በዚያው መጠን የምዘጋጅበት እውቀት ፈጥሮልኛል” ብሏል።
በመዝጊያ ዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች የሁዋዌ አይሲቲ አካዳሚ መምህራን፣ ተመራቂ ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል። ሲድስ ፎር ዘ ፊውቸር ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2008 በታይላንድ የተጀመረ ሲሆን ዓላማውም የሀገር ውስጥ የአይሲቲ ችሎታን ለማዳበር ነው።