አርእስተ ዜና
Thu. Apr 25th, 2024

ኢሰመኮ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ማጣራት እና ስለ ታሳሪዎች አያያዝ መግለጫ ሰጠ

Jul24,2020
ኢሰመኮ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ማጣራት እና ስለ ታሳሪዎች አያያዝ መግለጫ ሰጠ

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን አሳዛኝ ግድያ ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ ክልል፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና ሌሎችም አንዳንድ ቦታዎች የተከሰተውን መጠነ ሰፊ የጸጥታ ችግር ፣ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት ውድመት በሚመለከት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመነሻው ጀምሮ በቅርብ መከታተሉን የቀጠለ ሲሆን፤ እስከ አሁን የተካሄዱትና በመካሄድ ላይ ያሉት ዋና ሥራዎች የሚከተሉትን ይጨምራሉ፡-

1. የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በፈጣን ምርመራ ማጣራትና መዘገብ

ምንም እንኳን የደረሰውን አደጋ በተመለከተ በተወሰነ መጠን በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙሃንና ድርጅቶች እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መንግሥት የተዘገበ ቢሆንም፤ ኢሰመኮ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የምርመራ ስልት ላይ የተመሰረተና በበቂ ማስረጃዎች የተደገፈ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹን አይነት በተገቢው መጠን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን አዋቅሮ ወደ ሥራ አሰማርቷል፡፡

ምርመራው እስከ አሁን ድረስ በተደረገው ቅድመ ጥናት ሰፊ ችግር የተከሰተባቸው ተብለው በተለዩ 15 ቦታዎች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚካሄድ ሆኖ በተጨማሪም አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎች መጠነኛ ችግር በተከሰተባቸው ወደ 40 የሚሆኑ ቦታዎች ላይም ስለ ደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጠቃላይ መረጃ የሚሰበስብ ይሆናል፡፡ የምርመራው ውጤት የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓይነት፣ መጠን እና አዝማሚያ ለመለያት፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ የተጐዱ ሰዎች የሚካሱበትና መልሶ የሚቋቋሙበት እንዲሁም ይህን የመሰለ ጥሰት ደጋግሞ ከመከሰት ለመከላከል ስለሚያስችሉ እርምጃዎች ተገቢ ግብዓት እንደሚሆን እናምናለን፡፡ ስለ አደጋው ሁኔታ መረጃና ማስረጃ ያላቸው ሰዎች ወይም ድርጅቶች ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

2. ስለ እስረኞች አያያዝ ክትትል

አደጋውን ተከትሎ መንግሥት በወሰደው እርምጃ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል፡፡ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ ኢሰመኮ ስልታዊ ክትትል በማድረግ ላይ ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎችም የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ በተከታታይ ተመልክቷል፡፡

በተለይም እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና እስክንድር በቀለ በመጀመሪያ ላይ ታስረው ይገኙ የነበረበትን በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስር ያለውን እስር ቤት፣ እንዲሁም አሁን የሚገኙበትን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኘውን እስር ቤት በተጨማሪም በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ የሚባለው አካባቢ የሚገኘውን ጊዜያዊ የእስር ቤት ኮሚሽኑ ጐብኝቷል፣ ታሳሪዎችንና ኃላፊዎችንም አነጋግሯል፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ሰኔ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በአወጣው መግለጫና በተከታታይ ይሰጥ በነበረው የሚዲያ ማብራሪያ ላይ እንደተገለጸው በተለይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስር የሚገኘው ታሳሪዎቹ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎቹ በአንጻራዊነት እጅግም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው፣ የመታጠቢያና የንጽሕና ቤቶቹ ፅዳታቸው የተጠበቀና በአጠቃላይ አነጋገር የተቀባይነት ደረጃ ያላቸው መሆኑን ያስታውሳል፡፡

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ የእስር አያያዝ ላይ እንዲሻሻል ምክረ ሀሳብ የሰጠባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ መደረጋቸውን፣ እንዲሁም ከነገሩ ሁኔታ አንጻር በዋስትና መብት ሊለቀቁ ስለሚገባቸው የተወሰኑ ታሳሪዎች የሰጠው ምክር ሃሳብም በሚመለከታቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት ተግባራዊ መደረጉን በመልካም እርምጃነቱ እውቅና ይሰጣል፡፡

አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኰልን ጨምሮ ስድስት ታሳሪዎች አሁን የሚገኙበት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኘው እስር ቤትም ንፅሕናው የተጠበቀ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን የሚያገኝ፣ ታሳሪዎቹ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከቤተሰብ አቅርቦት የሚቀበሉበትና ለመተያየት የሚችሉበት፣ በአጠቃላይ አነጋገር ተቀባይነት ደረጃ ያለው ሲሆን፤ በተወሰነ መልኩ ከወቅቱ የአየር ጸባይና ከሕንጻው ባሕሪ የተነሳ የመቀዝቀዝ ጠባይ ያለው በመሆኑ ቅዝቃዜውን ለመቀነስ የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተመልክተናል፡፡

በዚህ እስር ቤት ካሉት ታሳሪዎች ውስጥ አቶ ሃምዛ ቦረና እና አቶ ሸምሰዲን ጣሃ የሕክምና ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን አቶ ሃምዛ ቦረና ከኮሚሽኑ ጉብኝት ማግስት ወደ ሕክምና የሄዱ ሲሆን አቶ ሸምሰዲንም በአፋጣኝ የሕክምና ጉብኝት እንደሚያገኙ ተረጋግጦልናል፡፡

በዚህ የእስር ቦታ በአጠቃላይ አነጋገር እና በአብዛኛዎቹ ታሳሪዎች እንደተገለጸልን ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን ተረድተናል፡፡

በሌላ በኩል ከታሳሪዎች የቀረቡትን መጠነኛ ቅሬታዎች ውስጥ ከቤተሰብ ጋር በተገቢው መጠን ተቀራርቦ ለመተያየት አለመቻሉ፣ የክፍሎቹ መቀዝቀዝ፣ የጸሐይ መቀበያ ጊዜ ማጠር፣ የመብራት መቋረጥ፣ የታሳሪዎች ለረጅም ጊዜ ለብቻ መቆየት የመሰሉ ችግሮች ሊሻሻሉ ስለሚችሉበት መንገድ ኮሚሽኑ ከኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ያደረገ ሲሆን አፈጻጸሙንም በቅርበት ይከታተላል፡፡

በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ የሚገኙ ታሳሪዎች ውስጥ የኦ.ኤ.ም.ኤን (OMN) ጋዜጠኞች የነበሩ አቶ ጉዬ ዋርዮ እና አቶ ሙሀመድ ሲራጅ፣ የኦፌኮ አባል አቶ ደጀኔ ጣፋ እንዲሁም ሶስት ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ አገር ዜጐች እና በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠለፋ ጉዳይ ተጠርጥረው የተከሰሱ ታሳሪዎችን ጨምሮ ሌሎች እስረኞችንም ኮሚሽኑ ጐብኝቷል፡፡

አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች በእስር ወቅትም ሆነ ወደ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያው ከመጡ ጀምሮ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳልተፈጸመባቸው፣ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያው ውስጥ የእስር አያያዙ በአጠቃላይ አነጋገር መልካም ቢሆንም በተለይ ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት አንጻር ከፍተኛ አስጊ ሁኔታ መኖሩን፣ የንፅሕና መጠበቂያና የመከላለያ ቁሶች አቅርቦት እጥረት መኖሩን፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ብዙ ሰዎች በመኖራቸው እያደገ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ሥጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ከቤተሰብ መገናኘትን በሚመለከት የተወሰኑ ታሳሪዎች ገና ከቤተሰብ ያልተያዩ መሆኑንና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ታሳሪዎችም በውጭ አገር የሚገኙ ቤተሰቦቻቸውን ገና በስልክ ለማነጋገር ዕድል አለማግኘታቸውን ገልጸውልናል፡፡ እነዚሁ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ታሳሪዎችም ዘግይቶም ቢሆን ከአገራቸው ኤምባሲ ኃላፊዎች ጋር መገናኘት መቻላቸውን አረጋግጠውልናል፡፡

አንድ ታሳሪ በእስር ወቅት ፖሊስ ተገቢ ያልሆነ እንግልት እንደፈጠረባቸውና በጥፊና በእርግጫ እንደመታቸው እንዲሁም ሁለት ታሳሪዎች በኦሮሚያ ባሕል ማዕከል ውስጥ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት አጠቃላይ ሁኔታው አስፈሪና አስጨናቂ እንደነበር፣ እንዲሁም በቁጥጥር ስር በዋሉበት የመጀመሪያው ቀን ምሽትና አዳር ያለ ምግብ፣ ውሃ እና የብርድ ልብስ ኮሪደር ላይ ለማሳለፍ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በአንጻሩ በቁጥጥር ስር ከዋሉና በተለይም አሁን ወደሚገኙበት ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ከመጡ በኃላ የእስር አያያዙ የተሻሻለ መሆኑን፣ ፖሊሶቹም በከፍተኛ የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በተማሪዎች እገታ ጉዳይ ተጠርጥረው የታሰሩት ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በኦሮሚያ ክልል ደምቢዶሎ ከተማ ታስረው በቆዩበት ወቅት የተማሪዎቹን ጠላፊዎች ታውቃላችሁ በሚል ጥርጣሬ በተደጋጋሚ እንደተደበደቡ፣ እንደተገረፉ፣ በሽጉጥ የማስመሰል ግድያ (Mock Execution) እንደተፈጸመባቸው የገለጹ ሲሆን፤ በአንጻሩ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ከመጡ ጀምሮ ምንም ዓይነት ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንዳልተፈጸመባቸውና ጠቅላላ የእስር አያያዛቸውም መልካም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች ውስጥ ሁለት ታሳሪዎች ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም እስከ ጉብኝቱ ቀን ድረስ ገና አለመለቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮችና በተለይም የተወሰኑት ታሳሪዎች በኦሮሚያ ክልል ደምቢዶሎ ከተማ እስር ወቅት ተፈጽሟል የተባለውን ድብደባ እና የማሰቃየት ድርጊት የሚያጣራ ይሆናል፡፡

በአብዛኛዎቹ ታሳሪዎች የተነሳው ሌላው ተደጋጋሚ ቅሬታ የወንጀል ምርመራ የሚወስደው ጊዜ፣ ብዙ ታሳሪዎች ገና ቃላቸውን ያልሰጡና መርማሪ ፖሊስ ያላናገራቸው መሆኑ እና በተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ እንደተገነዘበው የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር አካላት እጅግ ውስን በሆነ የሰው እና የፋይናንስ አቅም በርካታ ጉዳዮችን በማጣራት ከፍተኛ የሥራ ጫና ያለባቸው ቢሆንም በተቻለ መጠን የምርመራ ስራውን ማቀላጠፍ እና በዋስትና መብት ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች በአፋጣኝ መለየት ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ታሳሪዎች በሚመለከት ኮሚሽኑ በቅርቡ ለመመልከት በዝግጅት ላይ ያለ ቢሆንም፤ ብዙ ታሳሪዎች ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ በተሟላ ሁኔታ ያለወቁ በመሆኑ ሁሉም ታሳሪዎች ለቤተሰቦቻቸው ያሉበትን ቦታ በስልክ እንዲያስታውቁ እንዲደረግ ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል፤ አፈጻጸሙንም ይከታተላል፡፡

በተለይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ብዙ አባሎቻቸው እና የፖለቲካ ፖርቲዎቹ አመራሮች እንደታሰሩና ያሉበትን ቦታና ሁኔታ ለማወቅ አለመቻላቸውን ለኮሚሽኑ ያሳወቁ ሲሆን፤ ሁሉም የፖሊስ ኮሚሽን አባላት በቁጥጥር ስር የሚያደርጓቸውን ታሳሪዎች ወዲያውኑ ለቤተሰባቸው ያሉበትን ቦታ በስልክ እንዲያሳውቁ ሊደረጋ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ያሳስባል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የታሳሪዎች ጉዳይን በሚመለከት በሰጡት አስተያየት “አሁን በአለው የሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ፤ ፖሊስና ዐቃቤ ሕግ በቅድሚያ ትኩረት ሊያከናውኑ የሚገባው ጉዳይ፤ ሁሉም ታሳሪዎች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ በማናገር የአሉበትን ቦታ ማሳወቃቸውን ማረጋጥ እና በተፋጠነ ምርመራ በዋስትና መብት ወይም በነጻ ሊፈቱ የሚገባቸውን ታሳሪዎች በመለየት በአፋጣኝ መለቀቃቸውን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል፡፡

Related Post