Site icon ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ

አፍሪካ ከኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይል ልማቶች ልምድ ትቅሰም ተባለ

አፍሪካ ከኢትዮጵያ ታዳሽ ሃይል ልማቶች ልምድ ትቅሰም ተባለ

በመኮንን ተሾመ / አቡ ዳቢ – ለአለም አቀፉ የታዳሽ ሃይል ኤጀንሲ (ኢሬና) ፣ International Renewable Energy Agency (IRENA) ፣ ጠቅላላ ጉባኤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዋና ከተማ አቡዳቢ የተገናኙ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለሙያዎችና የፖለቲካ መሪዎች ኢትዮጵያ በራስ አቅም ከሰራቻቸዉ የታዳሽ ሃይል ልማቶች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድ እንዲቀስሙ ጥሪ አቀረቡ።

ባለሙያዎችና የፖለቲካ መሪዎች ጥሪያቸዉን ያቀረቡት ትላንት እ.አ.አ. ጥር 12 ቀን 2025 የኤጀንሲው 15ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ አቡ ዳቢ በተከፈተበት ወቅት ሲሆን በተለይ የታላቁን የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብን ግንባታ በራስ የገንዘብ አቅም ጀምሮ ማጠናቀቅ መቻሉ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደ ትልቅ ትምህርት ሊወሰድ እንደሚገባ በመጠቆም ነዉ።

የሴራሊዮን የአየር ንብረት ለውጥ፣ ታዳሽ ኃይል እና የምግብ ዋስትና ፕሬዝዳንታዊ ኢኒሸቲቬ ሊቀመንበር ዶ/ር ካንዴህ ዩምከላህ እንዳሉት የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ መድረስ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብና በተባባረ ክንድ በመስራታቸዉና በአፍሪካ ባልተለመደ ሁኔታ በራስ አቅም ለግንባታዉ የሚያስፈልገዉን ወጪ በመሸፈናቸዉ ነዉ።

ከአዘርባጃኑ የአለማቀፍ የአየር ለዉጥ ጉባኤ ተከትሎ ትልቅ የተባለዉ የ15ኛዉ የአለም አቀፉ የታዳሽ ሃይል ኤጀንሲ ጠቅላላ ጉባኤ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋና ከተማ አቡ ዳቢ እየተካሄደ ነዉ

ይህም የአፍሪካ ሀገራት ቁርጠኝነቱ ካለ በራስ አቅም በርካታ የታዳሽ ሃይል ልማቶች ማከናወን እንደሚቻል ሁነኛ ማሳያ ነዉ ሲሉ ዶ/ር ካንዴህ አብራረተዋል።

በጋና የኢነርጂ ሚኒስቴር የታዳሽ ሃይል ዳይሬክተር ሴዝ አግቤቭ ማሁ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት የአትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከህዝቡ እንዲሰበሰብ በማድረግ በራስ አቅም የታዳሽ ሃይል ልማት ማለትም በአፍሪካ ትልቁ የሆነዉን የታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ገንብተዉ ማጠናቀቃቸዉ እንደ ተአምር የሚታይ ነዉ ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በመሆኑም በራስ አቅም የታዳሽ ሃይል ልማቶች ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል። አክለዉም የአንችልም መንፈስን ካስወገዱና ያላቸዉን ሀብት ማሰባሰብ ከቻሉ አፍሪካዉያን በራስ አቅም በርካታ ፕሮጀክቶችን ማከናወን እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ የዉሃና የኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ አቶ ጎሳዬ መንግስቴ በወቅቱ ጉባኤዉ ላይ በመገኘት እንዳስረዱት ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ መርሃ ግብርን በአግባቡ በመተግበር ዓለም አቀፋዊ ግዴታዋን በግንባር ቀደምትነት እየተወጣች ነው።

እ.አ.አ በመስከረም 2023 በናይሮቢ ኬንያ በተደረገዉ ጉባኤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የአፍሪካን የታዳሽ እምቅ ኃይል የሚያለማ አጋርነት አስተዋውቃለች። ሀገሪቱ ከአፍሪካ ጋር ዘላቂ ኃይል ለማልማት የሚያስችል አዲስ ስልታዊ አጋርነት ይፋም አድርጋለች። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት 34 ቢሊዮን ዶላር ከሀገር ውስጥ እንደምታሰባስብም ቃል ገብታለች።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው 15ኛው የኢሬና ምክር ቤት በኢነርጂ ሽግግሩ ላይ ሰፊና ዘርፈ ብዙ ትብብርን ለማጠናከር ከኢሬና 170 አባል ሀገራት የተውጣጡ ሚኒስትሮችን እና ከፍተኛ ተወካዮችን ፣ምሁራንን ፣ ልማት ባንኮችን ፣ ዋና ስራ አስፈፃሚዎችን እና ወጣቶችን ሰብስቧል። ከጥር 12-18 በአቡ ዳቢ የሚካሄደውን የ2025 ጉባኤ “የአቡ ዳቢ የዘላቂ ሀይል ልማት ሳምንት” በሚል መርህ ጀምሯል።

ነገ የሚጠናቀቀዉን የኤጀንሲው 15ኛ ጠቅላላ ጉባኤን ተከትሎ ተሰብሳቢዎቹ በቀጣዮቹ ሶስት ቀናትም “የመጪዉ ጊዜ የሃይል አማራጮች ጉባዔ” /World Future Energy Summit/ የተሰኘዉን ዋነኛ አለማቀፍ ጉባዔም እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል።

Exit mobile version