Site icon ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ

ታጥቦ የማይፀዳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ?

ታጥቦ የማይፀዳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንት እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ

በግርማቸው እንየው – አቶ መላኩ ፈንታ በአመራር ብቃት የተመሰከረለዎት ነዎት። ይህንንም በተግባር ተፈትነው አስመስክረዋል። ለዚህ ደግሞ አልማ እና አማራ ባንክ ላይ የሰሩት ስራ ምስክር ናቸው። ዛሬ ይህንን ቦታ ቢያጡትም ነገ ምንም አይጠራጠሩ ተመልሰው ይይዙታል። የእርስዎ ቦታ ፊፋ እና ካፍ ነው። በትክክለኛው መንገድ ምንም ሳይጎድልብዎት ስፖርቱን ላግዝ ብለው መምጣተዎት ብቻ ያስመሰግነዎታል።

እውነት እንነጋገር ከተባለ ለዚህ ለተጨማለቀ ፌዴሬሽን አሳምረው ይበዙበታል። የእግር ኴስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ቦታ የሚፈልገው የአመራር ክህሎት እና ብቃት እንጂ እርስዎ በመግለጫወት ወቅት እንዳሉት ዘጠኝ ቁጥር ቦታ ላይ እንዲጫወቱ ፣ አለያም አሰልጣኝ እንዲሆኑ ወይም ዳኛ እንዲሆኑ አይደለም።

በአመራር ብቃት ደግሞ ከአንድም ሁለት ጊዜ እንደ ወርቅ ተፈትነው ነጥረው ወተዋል ። የፋሲል ከነማ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም የሰሩት ታሪክ ሁሌም ይታወሱበታል። አምስት አመት ያለምንም ጥፋት አማራ ስለሆኑ ብቻ ሙስና በሚል ታርጋ ቢታሰሩም ከእስር ወጥተው ሞራለዎት ሳይሰበር ህዝቤን ላገልግል ብለው ቀን ከሌት በታላላቅ ፕሮጀክቶች እየለፉ ይገኛሉ። ለዚህም ክብር ይገባዎታል።

ይህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ አሳፋሪ ጠቅላላ ጉባኤ ነው። ይህ ጠቅላላ ጉባኤ የፌዴሬሽኑ የህግ አማካሪ አቶ ሀይሉ ሞላ የምርጫ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሆኑ እንኳን አሜን ብሎ የተቀበለ ራሱ ያወጣውን ህግ ጠንቅቆ የማያውቅ ጉባኤ ነው።

አቶ ሀይሉ ሞላ ዛሬ አሸናፊውን ሲገልፁ የነበራቸውን የደስታ ስሜት እንኳን መደበቅ አልቻሉም ። እጅግ ያሳፍራል። የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የመድን ስፖርት ቦርድ አባል አቶ መንግስቱ ፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ክለብ የቡድን መሪ አቶ በለጠ ዘውዴ ( በነገራችን ላይ ለአራተኛ ጊዜ ነው ዘንድሮ አስመራጭ ኮሚቴ የገቡት ፤ ህጉ ግን ከሁለት ጊዜ በላይ አይፈቅድም) እንዲሁም ወ/ሮ ረሂማ የድሬዳዋ ክለብ ስራ አስፈፃሚ አባል በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ ሲካተቱ እንዴት ብሎ ያልጠየቀ ጠቅላላ ጉባኤ ነው።

ህጉ ግን እንደማይፈቅድላቸው በግልፅ ተቀምጧል። የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው የመንግስት አካል ጣልቃ መግባት አይችልም እየተባለ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሲመረጡ አጨብጭቦ ያፀደቀ ጉባኤ ነው። አንድ የህግ ባለሙያ ግዴታ በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ መኖር እንዳለባቸው እየታወቀ ያለ ህግ ባለሙያ የተዋቀረ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ነው።

ይህ ጠቅላላ ጉባኤ አርባምንጭ ላይ የወሰነው እና ጎንደር ላይ እንዲደረግ የተስማምበት ውሳኔ ወደ አዲስ አበባ ሲቀየር ለምን ብሎ ያልተከራከረ አሳፋሪ ጉባኤ ነው። አጀንዳ እንኳ እንዲያዝ ሲጠየቅ ከ136 ድምፅ 30 ሰው ብቻ ሲደግፍ 106 ሰው አልደገፈውም ። አንዳንዶች በገንዘብ እጃቸው የሚጠመዘዝ፣ አንዳንዶች በዘር ቋት የሚያስቡ የአዕምሮ ድኩማን ያሉበት ጠቅላላ ጉባኤ ነው።

ከጠቅላላ ጉባኤው አንድ ቀን በፊት መዝገበ ስጋ ቤት ምን እንደተሰራ የማይታወቅ እንዳይመስላችሁ። የአማራ ክልሉ ስራ አስፈፃሚ እጩ ዶ/ር ዳኛቸው በድምፅ ሶስተኛ ሆኖ ለምን ምክትል ፕሬዝደንት ሆነ? መዝገበ ስጋ ቤት ቀድሞ ስራው ተስርቷል።

ዶ/ር ዳኛቸው በምን ሞራልህ ይሆን አማራ ክልል የምትገባው? የደቡብ ክልል ምክትል ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ደመላሽን ጨምሮ ማን ማን መዝገበ ስጋ ቤት ታዳሚ እንደነበር የፎቶ ማስረጃዎች አሉ። ይህ ጠቅላላ ጉባኤ ዶ/ር ወገኔን ፣ ኮሚሽነር ተስፋዬ ኦሜጋን እና አሰልጣኝ አስራት ሀይሌን ያልመረጠ ስለ ስፖርት ምንም ግንዛቤ የሌለው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን አስመስክሯል። ለማንኛውም የመዝገበ ስጋ ቤቱ ሴራ ሲሳካ ፤ የማሪዮት ሆቴል ከሽፏል ። አቶ መላኩ ፈንታ ግን በንፅህናዎ ሊደሰቱ ይገባል ።

በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት አቶ ኢሳያስ ጅራ የሰሯቸው ጠንካራ ስራዎች ቢኖሩም ማረም ያለበዎት ጉዳዮችም አሉ። የተደረገበዎትን ጫና ለመቋቋም ያደረጉት ቢሆንም ከዚህ በኋላ ግን ለእንደዚህ አይነት ተግባር እንደ መዝገበ ስጋ ቤት አይነት ቦታ እንደማይገኙ ተስፋ አደርጋለሁ።

የመጀመሪያ ስራዎት ይህ አሳፋሪ ጠቅላላ ጉባኤ ፈርሶ በአዲስ መልክ የሚዋቀርበትን መንገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት መፍጠር ይኖርበዎታል። ምንም ሆነ ምን ከዚህ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው የሚወስናቸውን ውሳኔዎችም ሊያከብሩ ይገባል።

ለምሳሌ በእኔ እይታ የጎንደሩን መቀየርዎት በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም ። ከግል ውሳኔዎች መራቅ አለብዎት። ፌዴሬሽኑን ከጽ/ቤቱ ጀምሮ ማፅዳት ይኖርበዎታል። 95 ሚሊዮን ብር የወጣበት ህንፃ አራት አመት ሙሉ ስም ሳይዞር እስካሁን ቆይቷል። በየትኛውም የህግ አግባብ ይህንን ማስተካከል ይኖርበዎታል።

ብሄራዊ ቡድናችን በሜዳው እንዲጫወት የሀገራችን ሜዳዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መስራት አለብዎት ብዬ አስባለሁ። ከስራ አስፈፃሚዎችዎም ሆነ ከሊግ ካምፓኒው ጋር መልካም የስራ ግንኙነትን መፍጠር ተገቢ ነው። እኛም ጠንካራ ስራ ሲሰሩ ልናሞግሰዎት ሲሳሳቱ ልናርምዎት ተዘጋጅተናል።
መልካም የስራ ጊዜ ይሁንልዎት!!

Exit mobile version