የየካቲት 12 መታሰቢያ በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ የሰማዕታት ሃውልት በዛሬው እለት ታስቦ ውሏል።
የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ እለት የኢትዮጵያውያን የአንድነትና አይበገሬነታቸው አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ የጥንት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ተናገሩ፡፡ እለቱ ዛሬ የሚታወሰው የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሦስት ቀናት ውስጥ በፋሺስት ጣልያን ወታደሮች መጨፍጨፋቸውን ተከትሎ ነው።
በ85ኛው የካቲት 12 መታሰቢያ ስነ -ስርዓት ላይ የጥንት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መልእክት አስተላልፈዋል። በመልእክታቸውም እለቱ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሲሉ ከወራሪ ሃይል ጋር የተፋለሙና የተዋደቁ ጀግኖች የሚታወሱበት ልዩ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዘመኑ ጀግና ወጣቶች መካከል አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የአገሬን ሉዓላዊነት አላስደፍርም በሚል በፋሽስት ጣሊያን ወታደራዊ አዛዦች ላይ እርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል።
በመሆኑም የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ እለት የኢትዮጵያውን የአንድነትና አይበገሬነታቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል። እለቱ የሚታሰበው ለኢትዮጵያ ሲሉ በጀግንነት ገድል የፈፀሙትን እንዲሁም በፋሽስቱ ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉትን በማስታወስ ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም የቀደሙ አያቶች ያስከበሯትን አገር ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት ሲሉም አክለዋል። የመታሰቢያ በአሉ የሚታወሰው የአሁኑ ትውልድም አገሩ እንዴት እንደቆመች ለማስተማር መሆኑን ገልጸዋል።
በዕለቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሙዜና አልቃድር፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡
(ምንጭ – ኢዜአ)