Site icon ኒው ቢዝነስ ኢትዮጵያ

በባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥ ነግሣ የነበረች ቅድስት አገር

በባብ ኤል ማንዳብ ወሽመጥ ነግሣ የነበረች ቅድስት አገር

ኢትዮጵያ:-በ“ኢትዮጵያ”፣ንጋት፣ምጽዋ ኮከብ፣ ጣና፣ ንግሥተ ሳባ፣ ላሊበላ፣ ነጻነትና አብዮት መርከቦቿ ትታወቅ ነበር። ጌታቸው ወልዩ (ከሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ) – አንድ በዐረቦች ዘንድ የሚነገር ጥንታዊ አፈ-ታሪክ አለ። ይህ አፈ-ታሪክ “አፍሪካና እስያ አንድ አኅጉር ነበሩ!” ብሎ ይጀምራል። እናም! አፍሪካና እስያ ባልጠበቁት ሁኔታ በርዕደ-መሬት (የመሬት መንቀጥቀጥ) ክፉኛ ተንዘፈዘፉ፤ ተርገፈገፉ፤ ተንቀጠቀጡ፤ ተናወጡ። በመንዘፍዘፉ ኀያልነትና በመናወጡ ብርታት የተነሳ፤ እስያ ከአፍሪካ ተነጠለ።

አፍሪካ ከእስያ ተገለለ። እስያ ሳይወድ በግዱ በውስጡ ሀዘን እንደ ታመቀ፤ አፍሪካን ተነጠቀ፤ በቅርብ ሆኖ አፍሪካን እየናፈቀ። በዚህ መካከል በቀላሉ ያልተገመተ፤ አሳዛኝ ሁኔታ ተከሰተ።

ይኸውም፦ በአፍሪካና እስያ መካከል በተፈጠረ፤ ለጊዜው ድርጊቱ በተመሰጠረ የባህር ወሽመጥ ውስጥ፤ አያሌ ነፍሶች ገብተው ሰመጡ። በባህር ወሽመጥ (ሸለቆውም) ተዋጡ። እናም! የእስያ ዓይኖች በእምባ ተሞሉ። የእምባ ዘለላዎች በእስያ እምባ መስኮቶች ደጃፍ ተንጠለጠሉ። ቀጥሎም (ለጥቆም)፦ የእምባ መስኮቶቹ ተከፈቱ። የእምባ ዘለላዎቹም ቁልቁል ተመለከቱ፤ የእምባ ጠብታዎችን እያመረቱ።

ይኸኔ እስያ ቀጭኑን የባህር ወሽመጥ እያየች፤ የእምባ ጎርፍ አወረደ/ች። እምባዋን ዘረገፈች። እምባዋን ዘራች። የሀዘን እንጉርጉሮ (lament) አሰማች። በእምባው ብዛት የተነሳም የባህር ወሽመጡ መግቢያ በእንባ ተደለደለ። ዓለምን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ጉድ አስባለ። መጠሪያ ስሙም “ባብ ኤል ማንደብ” ተባለ። አሁን በዚህ እምባ በበዛበት፤ ለቅሶ በነገሠበት፤ ሀዘን በደራበት፤ የባህር ወሽመጥ ወይም የባህር ሸለቆ አሊያ የባህር ሰርጥ ማን ደፍሮ ይጓጓዛል? ተባለ፤ አዎ! ተባለ፤ ክስተቱ አያሌዎችን በፍርኃት እንደ ሸበለለ።

ዐረቦችም “የባብ ኤል ማንደብ” አፈ-ታሪክኛ አፈጣጠር ክስተት ግራ አጋብቷቸው፤ የጉዞው ሁኔታ አስፈርቷቸው፤ መጠሪያ ስሙን ከመንስኤውና ሰበቡ ጋር እያዛመዱት፤ “ለጉዞ የማያስተማምን ወሽመጥ” (strait’s precarious navigation) አሊያ “የእንባዎች መግቢያ በር” (The Gate of Tears) ሲሉ ጠሩት።

ይኸው ጉደኛው “የባብ ኤል ማንደብ” በስመ-ሀዳሪ እምባን ኮርኳሪ ሆነና፤ በሀዘን መነሻ የሰው ሰውኛ የተፀውዖ ስምና የዳቦ ስም ተበጃጀለት፤ የሀዘን ማቅ ልብስ እየተዘጋጀለት። እናም! በእምባና ለቅሶ ባህር ሸለቆነት (ሰርጥነት) ስሙን እያስጠራ፤ “የለቅሶ መግቢያ በር” (Gate of Lamentation) ወይም “የሀዘን መግቢያ በር” (Gate of grief) ተብሎ ተጠራ።

እኔም ይህን አፈ-ታሪክ፤ በታሪክ ውሃ ልክ አስሬ፤ ዛሬ ለእናንተ ነገርኳችሁ። እናንተ ደግሞ በእውነትና ታሪክ ባህር ስትጓዙ፤ የእውነትና ታሪክ ሰነድ ስትመዙ፤ ከዚህ የሀዘን፣ የለቅሶና እምባ በር ማዶ ያለች አንድ ቅድስት አገር አለችና እንዳትረሱ፤ አደራ እላችኋለሁ በዚሁ የታሪክ ፍሰት እንድትገሰግሱ።

እናም አፍሪካና እስያ ሲለያዩ፤ በግራ በኩል -ቀይ ባህር፤ በቀኝ በኩል የኤደን ባህረ-ሰላጤ ይታዩ ጀመር። ተያይዞም እነዚህ ትላልቅ ሁለት የውሃ አካላትን የሚያገናኝ ጠባብ የውሃ መንገድ ተፈጠረ። ስሙም “የባብ ኤል ማንደብ” ወይም “የለቅሶ መግቢያ” (Gate of Lamentation) ተሰኘ።
በዐረቢኛ “ባብ ኤል ማንዳብ” (Bāb al-Mandab) ወይም በእንግሊዝኛና በአብዛኛው አጠራሩ “የባብ ኤል ማንዴብ ወሽመጥ” (Bab el-Mandeb Strait) ተብሎ የሚጠራው ቀጭን የባህር ሸለቆ (ሰርጥ)፤ በዐረቢያ (በሰሜን ምሥራቅ) እና በአፍሪካ (በደቡብ ምዕራብ) በኩል የሚገኝ ሲሆን፤ ቀይ ባሕርን (በሰሜን ምዕራብ) ፤ ኤደን ባህረ-ሰላጤን እና ሕንድ ውቅያኖስን (በደቡብ ምስራቅ) የሚያገናኝ ሁነኛ የባህር መስመር ሆነ።

እናም! ከዚሁ “የባብ ኤል ማንዴብ/ ማንዳብ ወሽመጥ” (Bab el-Mandeb Strait) አቅራቢያ ሀዘንተኛን/ ለቀስተኛን የምታጽናና፤ በሃይማኖታዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ አፈ-ታሪካዊ፣ ታሪካዊና ሥልጣኔያዊ ዕይታዎች ስመ-ገናና የሆነች፤ በጥቅሉ በሃይማኖትና ሳይንሱ ዓለም “የተቀደሰች ምድር” (Ethiopia: A Holy Land for Religion and Science) የምትሰኝ፤ አንድ ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ምስጢራዊና ተአምራዊ አገር ከቀይ ባህር ምዕራብ አቅጣጫ ላይ በክብር አለች። ይህችም አገር ኢትዮጵያ ነች።

ታዋቂው የፑልቲዘር ዶት ኦርግ በበኩሉ የሥነ-ቅርስ ሕይወትና የዝግመተ-ለውጥ ሥነ-ሕይወታዊ ባለሙያዎችን ጠቅሶ ኢትዮጵያን “ቅድስት ምድር” በማለት የመጥራቱ ምስጢር አፈታት ከዚሁ ይመነጫል። (Ethiopia is a Holy land to paleontologists and evolutionary biologists. (Pulitzer center.org) መቼም ፑልቲዘርን የማያውቅ ጋዜጠኛ ለክኂለ-ተግባቦትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ይኖራል ብዩ አላምንም።

በተመሳሳይ ከቀይ ባህር ምሥራቅ አቅጣጫ የምትገኘውን ጥንታዊ አገር “የመን” ደግሞ፤ ጻድቁ ኖኅ “የወተትና ማር ምድር” ሲል ጠርቷት ያውቃት እንደ ነበር ቅዱሱ መጽሐፍን ዋቢ የሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። (According to the Bible, Noah knew it as “the land of milk and honey)”

እንግዲህ “ባብ ኤል ማንዳብ” (Bāb al-Mandab) ወይም “የባብ ኤል ማንዴብ ወሽመጥ” (Bab el-Mandeb Strait) “ለቅድስቲቱ ምድር” ኢትዮጵያና ጻድቁ ኖኅ “የወተትና ማር ምድር” ላላት የመን (ደቡብ ዐረቢያ) ቅርብ ነው ማለት ነው።

ሳይንሱም ቢሆን “የቴክቶኒክ ኀይሎች (tectonic forces) የዐረቢያን ልሳነ-ምድር (ውሃ ገብ መሬት) ከአፍሪካ ወደ ላይ ሲገፉት አዲስ የመሬት ቅርጽ ተፈጠረ” ነው የሚለው።
ቴክቶኒክ ኀይሎች” (tectonic forces) ማለት ደግሞ፦ የባህር ዳርቻዎች አካባቢን የሚመለከቱ ሲሆን፤ ከምድር ውስጥ በሚመነጩ ኃይሎች አማካይነት የመሬትን የላይኛው ንጣፍ ክፍል የመግፋት፣ የማንቀሳቀስና የቅርጽ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ማለት ነው።

በዚህም መሠረት:- በሥነ-ምድራዊ ዑደት አማካይነት፤ በቴክቶኒክ ኀይሎች ተገፍቶ በወጣው የዐረቢያን ውሃ ገብ መሬትና አፍሪካ መካከል፤ ከረዥም ጊዜ በኋላ የውሃ አካል ሊፈጠር ቻለ። እናም በግራ በኩል ቀይ ባህር በቀኝ በኩል የኤደን ባህረ-ሰላጤ ይታዩ ጀመር። ተያይዞም እነዚህ ትላልቅ ሁለት የውሃ አካላትን የሚያገናኝ ጠባብ የውሃ መንገድ ተፈጠረ። ስሙም “የባብ ኤል ማንደብ” ወይም “የለቅሶ መግቢያ” (Gate of Lamentation) ተሰኘ።

የባብ ኤል ማንዳብ ለሁለት የሚከፍለው ደሴት ያለው ሲሆን “የፔሪም ደሴት” ይሰኛል። የፔሪም ደሴት የምሥራቅ መተላለፊያ (ቻናል) “የአሌክሳንደር (እስክንድር) ወሽመጥ” ተብሎ ይጠራል። ስፋቱም 3 ማይል (3 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር) ነው ፡፡ የፔሪም ደሴት ምዕራባዊው ሰርጥ ደግሞ “ዳክት-ኤል-ማዩን” በመባል ይታወቃል። ስፋቱ 16 ማይል (25 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር) ነው።

እናም ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ቀይ ባህር ላይ ኀያል ድርሻ በነበራት ዘመን፤ የባብ ኤል ማንዳብን ተሻግረው በቀይ ባህር በኩል ወደ ስዊዝ ቦይና መካከለኛው (ሜዲቴራኒያን) ባህር፣ መካከለኛው ምሥራቅን ጨምሮ ወደ እስያ፣ አውሮፓና አሜሪካ የሚሸጋገሩ፤ በቀይ ባህር ደቡብ አድርገው ወደ ኤደን ባህረ-ሰላጤና ሕንድ ውቅያኖስ ለሚያመሩ መርከቦች እና በቀጣናው በባህር ትራንስፖርት ንግድ (maritime trade) ረገድ ይደረግ ለነበረው እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራት።

በተለይ “ባብ-ኤል ማንደብ”፦ በየመን ዐረቢያን ልሳነ-ምድር (ውሃ ገብ መሬት) እና በአፍሪካ ቀንድ አገሮቹ:- ቀደም ሲል ኢትዮጵያ እነሆ ኤርትራና ትንሿ አገር ጅቡቲ መካከል የሚገኝ፤ ቀይ ባህርን ከኤደን ባህረ-ሰላጤና ሕንድ ውቅያኖስ ጋር የሚያገናኝ፤ በቀይ ባህር በኩል ወደ ስዊዝ ቦይና በስዊዝ ቦይ አውሮፓ፥ እስያና አሜሪካ ለሚደረግ የባህር ጉዘት ትልቅ ድርሻ ያለው፤ በቀን ስልሳ (60) ያህል መርከቦች የሚተላለፉበት ቁልፍ የባህር ወሽመጥ ከመሆኑ አንጻር፤ ከነበረው ቅርበት፣ አመቺነትና ስትራቴጂያዊ ወደብነት አኳያ፤ የያኔው የኢትዮጵያ አሰብ ወደብ ድርሻው የላቀና እጅግ አዋጭ ወደብ ነበር። (አሁንም በአግባቡ ከተጠቀሙበት አዋጭ ወደብ ነው።)

ይኸውም የባብ ኤል ማንዳብ ሸለቆ፤ በቀጣናው ጂኦ-ፖለቲካ ኮክቴልነቱ የተነሳ፤ “ዓለም አቀፍ” የተሰኙ የበርካታ አገሮች መርከቦች የሚጓጓዙበት፤ በቀን ወደ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ዘይት በመርከብ ተጭኖ የሚተላለፍበት፤ የኢትዮጵያ ባህር ኀይል ቤዝን ባለመኖሩ የተነሳ ቀጣናው የተደፈረበት፤ በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉ እጅግ የሰፋበት የባህር ሰርጥ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።

እንደሚታወቀው አሰብ ከ1983 ዓመተ ምህረት በፊት:- የኢትዮጵያ ባህር ኀይል ቤዝን ጨምሮ የኢትዮጵያ ሠራዊት (ምድርና አየር ኀይሎች)፤ ፖሊስ፣ ሌሎች የፀጥታና ደኅንነት ኀይሎች የከተሙበት፤ ቁልፍ ወታደራዊ ስፍራ ነበር።

ለዚህ ዋቢነት በርካታ የቀድሞ ኢትዮጵያ ባህር ኀይል አባላትን ጨምሮ በርከታ ወታደራዊ ባለሙያዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካዊ፣ ጂኦ-ምጣኔ ሀብታዊና ጂኦ-ወታደራዊ ተንታኞችና የጦር ዘጋቢ ጋዜጠኞች እንደሚጠቅሱት፤ ቀደም ሲል የአሜሪካ ባህር ኀይል የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ ንብረት የነበረችውና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር በ1962 ለኢትዮጵያ ባህር ኀይል በውሰት (ስጦታ) የተሰጠችው “ኢትዮጵያ” (ኤ -101) የማሰልጠኛ የጦር መርከብን ጨምሮ ንጋት፣ ምጽዋ ኮከብ፣ ጣና ሐይቅ፣ ንግሥተ ሳባ፣ ላሊበላ፣ ነጻነትና አብዮት የመሳሰሉ የኢትዮጵያ መርከቦች፤ እንኳን ለኢትዮጵያ ለቅርብ ተጎራባቾቹ ለጅቡቲ፣ የመንና ቀጣናው ትልቅ ዋስትናዎችና የኩራት ምልክቶች ነበሩ።

ለዚህም ነው አሰብ የኢትዮጵያ ግዛት በነበረችበት ዘመን የንግድ ባለሙያ በመሆኑና ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አመታት በመኖሩ አሰብን በተደጋጋሚ የማየት ዕድሉ ለገጠመው አንድ የመናዊ፤ አንድ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ሲል ጠየቀው። “What were your favorite Ethiopian ships before May 1991?“ (እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ቀመር ከላይ 1991 ማለትም ከግንቦት 1983 ዓመተ-ምህረት በፊት ላንተ ተወዳጅ የነበሩ የኢትዮጵያ መርከቦች እነ ማን ነበሩ?)

ለኢትዮጵያ እጅግ የገዘፈ ፍቅር ያለው ይኸው የመናዊ እጅግ በሚገርም ሁኔታ “My favorite ships at that time were ” Ethiopia” (A-101), “Queen Sheba”, ” Lalibela”, “Lake Tana”, ” Nigat”, “Mitsewa Kokeb”, “Abiyot /Revolution, and Netsanet /freedom)” እያለ በአስገራሚ ሁኔታ ምላሽ ሰጠ።

በሁኔታው የተገረመው ኢትዮጵያዊው የመናዊውን ልክ እንደ ቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኀይል ባልደረባ ቆጠረውና “What was the name of your warship?” (የነበርክበት ጦር መርከብህ ስም ማን ይባላል?) በማለት ጠየቀው።

የመናዊውም ተገረመና “I went to Ethiopia several times. I was not the previous Ethiopian Navy sailor. I was a merchant.” በማለት መልስ ሰጠ። የመናዊው ያለው፦ “ወደ ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜያት ሄጃለሁ። ይሁንና እኔ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኀይል መርከበኛ አልነበርኩም። እኔ ነጋዴ ነበርኩኝ፝።“

መታወቅ ያለበት ከኤደን ባህረ-ሰላጤና ከሌላው የእስያ አኅጉር ቀሪ ክፍል በባህር ትራንስፖርት ረገድ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የሚካሄድ የወጪ ምርት ወደ ግብጽ ስዊዝ ካናል (ቦይ) ከመድረሱ በፊት የግድ በባብ ኤል ማንደብ መተላለፍ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በነበራት የቀድሞ ባህር ኀይሏ ጥንካሬ የነበራት የቀጣናውን ደኅንነትና ሰላም የማረጋገጥ ድርሻ የጎላ ነበር።

የባብ ኤል ማንደብን ቁልፍ የባህር መተላለፊያነት ለመረዳት የሚከተለውን የሮይተርስ ዘገባ መመልከት ይቻላል። በዘገባው መሠረት:- እንደ ጎርጎሳውያኑ ቀመር በ2008 ላይ ብቻ 4 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ፤ በ2009 ደግሞ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ፤ በዚሁ የውሃ አካል ላይ ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካና እሰያ ተጓጉዟል። በዚህም መሠረት:- 1 ነጥብ 8 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ወደ ስዊዝ ቦይ ያመራው በዚሁ የባብ ኤል ማንደብ ወሽመጥ በኩል ነበር።

በአሁኑ ጊዜም ግብጽን ጨምሮ ከእውነት የሸሹ እንደ ኢትዮጵያ አኩሪ የሥልጣኔ ታሪክ የሌላቸው በርካታ ምዕራባውያን ኀያል አገሮችና አንዳንድ የዐረቡ ዓለም መንግሥታት፤ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም በመያዝ፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታን ከተቻለ ለማስተጓጎልና የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለመመለስ እያደረገች ያለው ጥረት ላይ ያለ የሌለ ዘመቻ አድርገው ጫና በማሳደር እንቅፋት የሚፈጥሩት፤ “ከቀይ ባህር ምዕራብ አቅጣጫ ላይ በክብር የተቀመጠች” የተባለችውን፤ በሃይማኖትና ሳይንሱ ዓለም “የተቀደሰች ምድር” (Ethiopia: A Holy Land for Religion and Science) የተሰኘችውን፤ ጥንታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ምስጢራዊና ተአምራዊ አገር ኢትዮጵያ መልካም ስም ለማጠልሸት፤ ከተቻለ ለማናጋት ከመፈለግ ነው።

ለዚህም ነው በተለይ ኢትዮጵያ ታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረተ- ድንጋይ ካስቀመጠችበት ዕለት አንስቶ፤ ነግቶ በጠባ ያለ እረፍትና ሀፍረት፤ ፀረ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎችን (Anti-Ethiopia and Ethiopians propaganda campaigns) እያካሄዱ የሚገኙት፤ “መንግሥትንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዳይረጋጉ (ከተቻለ ማፈራረስ)ና ማዳከም” (Destabilize and enervate governmental and non-governmental/ non-government organizations) የሚል የክፋትና የጥፋት ስትራቴጂ በግልጽና ግልጽ እያራመዱ የሚገኙት።

የሚገርመው ግን ጦርነትን እንደ ትርፍ ማግኛ የሚጠቀሙ ኀይሎች (ወዳጅ መሳይ አገሮችም አሉበት)፡ ኢትዮጵያ ድጋሚ ወደ ባብ ኤል ማንደብን ቁልፍ የባህር መተላለፊያ እንዳትቀርብ “ኢትዮጵያን ስቦ ካመጣት ቀይ ባህር ቀጣና ድጋሚ ማባረር” (The new expulsion of Ethiopia from the magnet Red Sea) የሚለው የክፋትና ተንኮል ስትራቴጂ አራማጅ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል።

ውድ ወገኖቼ፦ እነሆ በጥልቀት ከገባን አስፈላጊው ነገር፤ ደራሲ፣ አርበኛ፣ እንደ ኮኮብ አብሪው ባለቅኔ፣ ፀሓፊ ተውኔትና መምህር የነበሩት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ

“አገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፤
ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፤ የእንቧይ ካብ።“
በማለት ኢትዮጵያውያን እንዲተባበሩና እጅ ለእጅ ተያይዘው ለአገራቸው ክብር በጋራ እንዲቆሙ አሊያ እዳውና ችግሩ ከባድ እንደሚሆን ያስተላለፉትን ምክር አዘል ማንቂያና ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ነው። ለማንኛውም ኢትዮጵያ አገራችን ለዘላለም ትኑር! እግዚአብሔር አገረ-ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

Exit mobile version