የህጻናት ስርቆት በኢትዮጵያ

በመላኩ ብርሃኑ

እነዚህ 19 ህጻናት ከወላይታ ተሰርቀው በማዳበሪያ ታፍነው ወደ አዲስ አበባ ሲወሰዱ መንገድ ላይ ሳሉ ነው እግዚአብሄር የደረሰላቸውና የተረፉት!!

ገና ሳስበው ራሱ እጅግ የሚዘገንነኝ ወንጀል የህጻናት ስርቆት ወንጀል ነው። ያኔ ስራዬ ወንጀልን መዘገብ በነበረበት ጊዜ ያየኋቸው ዛሬ ድረስ የማይረሱኝ የተሰረቁ ህጻናት ጉዳይ ሁሌም ከእንቅልፌ የሚያባንነኝ ፍርሃት ነው የሚጭርብኝ።

ህጻናት ከቤተክርስቲያን፣ ከሰፈር፣ ከትምህርት ቤት፣ ከሚጫወቱበት ማንኛውም ስፍራ ነው የሚሰረቁት። ሰራቂዎቹ በአብዛኛው ሴቶች ናቸው። ድንገት እናት መስለው፣ ህጻናቱን አባብለው ፣ በነጠላ ሸፈን አድርገው ከስፍራው በብርሃን ፍጥነት እብስ ይላሉ።

ከዚያ በኋላ እግዚአብሄር ካልረዳ በቀር ወላጅ የተሰረቁ ልጆቹን የትም ፈልጎ አያገኛቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ልጆቹ ፍጹም በማይታወቁበት ሩቅ ስፍራ ስለሚወሰዱ ፣ ቢገኙም እንኳን ወላጅ እንኳን የገዛ ልጁን መለየት እስከማይችልበት ደረጃ ድረስ ስለሚጎዱ ነው።

ቢዘገንንም ከዓመታት በፊት በስራዬ አጋጣሚ በአይኔ ያየሁትን ልንገራችሁ። በጊዜው በጥቆማ መንገድ ላይ አይናቸው ጠፍቶ ሲለምኑ የተገኙት ህጻናት የታወሩት በተፈጥሮ አልነበረም። ሰራቂዎቹ የልጆቹን አይን በጋለ ወስፌ ወግተው ያፈርጡታል። ከብዙ ህመምና የቤት ውስጥ ቆይታ በኋላ ልጆቹ አይነስውር ሆነው ጎዳና ይወጣሉ።

በእንክብካቤ እጦት ጸጉራቸው ያድጋል፣ ህጻናቱን ከሴቶች የተቀበሉ ዋና ወንጀለኞች ልጆቹን መንገድ ላይ አውጥተው ያስቀምጧቸውና ከጠዋት እስከማታ ጸሃይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው እንዲለምኑ ያደርጓቸዋል። ወላጅ ራሱ በአጠገባቸው ቢያልፍ እነዚያ ልጆች የርሱ ልጆች ስለመሆናቸው የሚያውቅበት ምልክትም የለም።ያው ዓይን የአንድ ሰው ገጽታ ሙሉ መገለጫ ነው። ዓይን ሲጠፋ የሰው ገጽታም አብሮ ይቀየራል።

በእድሜ በጣም ህጻናት ከሆኑት ጋር አብራቸው እንድትለምን የምትደረግ እናት የምትመስል ሴትም የወንጀሉ ዋና ተካፋይ ናት። ወንጀለኞች ገንዘቡን ለራሳቸው ገቢ በማድረግ ሁሌም በልጆቹ ይነግዳሉ። ልጆቹ ሲያድጉ ግን ምን እንደሚያደርጓቸው እግዚአብሄር ይወቅ። ምናልባት እንዳገለገለና እንዳረጀ የጋሪ ፈረስ አውጥተው ይጥሏቸው ይሆን?

ብዙ ህጻናት ደግሞ ይደፈራሉ። በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ይበላሻል። ይኼ ደግሞ ለማውራትም እጅግ ያሳዝናል….ይቅር!!
ሌሎች ደግሞ ይሸጣሉ። አገልጋይ ይሆናሉ። በማያውቁት ሃገር ፣ ሊጠፉ በማይችሉበት ሁኔታ ሩቅ ስፍራ ላይ የሆነ አንድ ሰው ከባድ ስራ እያሰራ ህይወታቸውንና ጉልበታቸውን ይመዘብረዋል። ወይም የተለያየ ስራ እየሰሩ ገቢውን ለዚያ ‘ወንጀለኛ’ እየገበሩ ይኖራሉ። ጉልበት ብዝበዛ ይካሄድባቸዋል።

እንዲህ እንዲህ እያለ የነዚህ ልጆች ህይወት በዚያው ባክኖ ሲቀር ወላጆችም እስከዕለተ ሞታቸው አይናቸው በእንባ ርሶ ልጆቻቸውን እያሰቡ ያልፋሉ። በህይወትም በሞትም ተለያይቶ መቅረት …ለዚያውም ለወላጅ እና ለልጅ …ለዚያውም የተሰረቀ ሰው ኖረ ሞተ በማይባልበት ሁኔታ …አስቡት እስኪ!

የነዚህ ከላይ የምታዩዋቸው ህጻናት መሰረቅና ወደአዲስ አበባ መምጣት ዓላማም ከዚህ የተለየ ነው ብዬ አላስብም።ህጻናቱ ሲጮኹ ሰው ደርሶላቸው ተረፉ እንጂ ወንጀለኞቹ ሶስት ሴቶች ሲጠየቁ ከነርሱ ቀደም ብሎ የተሰረቁ ህጻናት የጫነ መኪና አዲስ አበባ መግባቱን ተናግረዋል።መኪናው የት ገባ? መኪና ሙሉ ህጻናቱስ የት ገቡ? የታወቀ ነገር የለም።ከዚህ በኋላም ወሬው አይወራም። ወላጅ ብቻ በየቤቱ እዬዬ እያለ ይኖራል።

የወላይታ አስተዳዳሪዎች ሆይ! የዚያ ክልል አክቲቪስቶችና ይመለከተኛል የምትሉ ሁሉ….
እባካችሁ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲጠብቁ አስተምሩ። ከማንኛውም እንዲህ አይነት ወንጀል ህጻናቶቻችሁን ጠብቁ። ወንጀል ፈጻሚዎቹም ከናንተው መሃል የወጡ ናቸውና ተከታትላችሁ ምንጩን አድርቁት። ስራውን እና ሃላፊነቱን በፖሊስ ላይ ብቻ ጥላችሁ አትቀመጡ። ለህዝባችሁ ከዚህ ያነሰ ነገር ልትሰሩለት አትችሉም።

እኛ ከተማ ያለን ደግሞ! …የእነዚህ ልጆች እጣ ነገም የኛ ልጆች እጣ ነውና በማንኛውም አጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ ህጻናትን መንገድ ላይ ወይም በልመና ተሰማርተው ካየን ቆም ብለን እንጠይቅ። ማነህ? ከየት መጣህ?ይህች ሴት/ይህ ሰው ምንህ ነው ብለን እንጠይቅ። እናንተ ስትጠይቁ ለመከላከል የሚሞክሩ ሰዎች ካሉ ነገር አለ ማለት ነው ። ለፖሊስ ጠቁሙ።

ልጆቻችሁንም ቢሆን የማያውቁትን ሰው እንዳይጠጉ አስፈሪ ታሪክ እየነገራችሁም ጭምር ቢሆን አስተምሯቸው።
ጎበዝ!! …ዛሬ ካልተባበርን ነገ “አፋልጉኝ!” ስንል መኖራችን ነው። በህጻናት የሚነግዱትን የሰይጣን ጋሻ ጃግሬዎች ግን የንጹሃን ህጻናት አምላክ

በእውነት ይፍረድባቸው!!
ገና ሳስበው እንባዬን የሚያመጣብኝ ህመም የልጆች ስቃይ ብቻ ነው።ሜርድ!!