የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያና ኤርትራ የደረሱትን የሰላም ስምምነት አደነቀ

የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያና ኤርትራ የደረሱትን የሰላም ስምምነት አደነቀ

Amharic

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላምና ወዳጅነት ስምምነትን ታሪካዊ በማለት አወደሰ።

ምክር ቤቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢፌዴሪ ዶክተር አብይ አህመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈራረሙት ስምምነት ለአፍሪካ ቀንድና ለመላው ዓለም ጠቃሚ ነው ብሏል።

በአጠቃላይ በሁለቱ ሀገራት መካካል አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑንም ገልጿል።

ምክር ቤቱ አስመራ ላይ የተደረሱ ስምምነቶችን በማንሳትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ተቋርጦ የነበረውን የስልክ ግንኙነት ማስጀመራቸው፣ ኤምባሲዎቻቸውን ለመክፈት በመወሰናቸው፣ የወደብ አገልግሎት ለመጀመር በማቀዳቸው፣ የሁለቱ ሀገራት አየር መንገዶች ወደ አስመራና አዲስ አበባ ለመብረር በመወሰናቸው እርምጃውን ይበል የሚያሰኝ ነው በማለት አወድሷል።

የምክር ቤቱ ሁሉም አባላት በመግለጫቸው ይህንን የሚያበረታታ የሰላም እርምጃ ስምምነቱን እንዲተገብር ከኢትዮጵያና ኤርትራ ጎን እንደሚቆምም አስታውቀዋል።

የተመድ ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የሁለቱ ሀገራት የሰላም ስምምነት ለሀገራቱና ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለምም ትልቅ ተስፋን ያጫረ እንደሆነ ማንሳታቸው ይታወሳል።

እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት የሰላም ስምምነታቸውን ዳር ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት የሚፈልጉትን ድጋፍ ሁሉ ለማቅረብ ድርጅቱ ዝግጁ መሆኑን ነው የገለፁት።

(በኤፍ.ቢ.ሲ)