ኤጀንሲው በአመቱ ከ7 ቢሊዮን ብር መድኃኒቶችን ለመግዛት አቅዷል

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በያዝነው በጀት አመት 7 ቢሊዮን 198 ሚሊዮን 758 ሺህ 604 ብር ወጪ ያላቸው በመደበኛ ወይም በተገላባጭ ፈንድ የሚቀርቡ መድኃኒቶችን እና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን ግዥ ለማከናወን ማቀዱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልገሎ ከሰራተኞች ጋር በነበራቸው ምክክር ወቅት አስታወቁ፡፡

4.6 ቢሊዮኑ ለመድኃኒት መግዣነት ሲውል ቀሪው ለኬሚካል፣ ዲያግኖስቲክስ እንዲሁም ለህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዥ እንደሚውል ተገልጿል፡፡ የማእቀፍ ግዥን በማጠናከር የህይወት አድንና መሰረታዊ መድኃኒቶች እንዲሁም የህክምና መገልገያዎች አቅርቦትን ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሰራ አብራርተው የመድኃኒት አቅርቦትን ማረጋገጥ ለኤጀንሲያችን የምርጫ ጉዳይ ሣይሆን የህልውና ጉዳያችን ነው በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊ የመረጃ ስርአት በመዘርጋት፣ ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር እና አቅራቢዎችን ክትትል በማድረግ መድኃኒቶች በሚፈለጉበት ጊዜ እንዲቀርቡ የፋይናንስ አጠቃቀማችንን ማሻሻል ላይ ልንረባረብ ይገባል በማለት አሣስበዋል፡፡ ከኮቪድ 19 እና ሌሎች ድንገተኛ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የድንገተኛ አቅርቦት ሰንሰለትን በማጠናከር ቀጣይነት ያለው የስርዓት ማሻሻያን ተግባራዊ በማድረግ የኤጀንሲውን ነባር አዋጅ እንዲሻሻል የቀጣይ ተግባራችን የትኩረት አቅጣጫዎች ይሆናሉ በማለትም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው በ2012 ዓ.ም 3.5 ቢሊዮን የመደበኛ፣ 12.9 ቢሊዮን የጤና ፕሮግራም በጥቅሉ 16.5 ቢሊዮን ብር ዋጋ የነበራቸውን መድኃኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን ለመላው የሀገሪቱ የጤና ተቋማት ማሰራጭት መቻሉን በመድረኩ መረዳት ተችሏል፡፡
(ምንጭ – የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ)