2 ግለሰቦች ሃሰተኛ የብር ኖቶችን ባንክ ወስደው ሊቀይሩ ተያዙ

Spread the love

ከ180 ሺህ ብር በላይ ሃሰተኛ የብር ኖቶችን ባንክ ወስደው ሊቀይሩ የነበሩ 2 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

ከ180 ሺህ ብር በላይ ሀሰተኛ ገንዘብ ኖቶችን ወደ ንብ ባንክ ወስደው ሊቀይሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ዛሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል። ሁለቱ ግለሰቦች በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መቐለ ሞሚና ቅርንጫፍ በታተመ እና እናት ባንክ አዲሃቂ ቅርጫፍ በታተመ ማሸጊያ የተጠቀለለ ከ180 ሺህ ብር በላይ ሃሰተኛ ገንዘብ ወደ ንብ ባንክ ወስደው ሊቀይሩ ሲሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ግለሰቦቹ የያዙትን ሃሰተኛ ብር ንብ ባንክ ካዛንቺስ ቅርጫፍ ካሉ ሰራተኞች ጋር 40 ከመቶ ለባንክ 60 ከመቶ ለራሳቸው ለማዋል ስምምነት አድርገው ከመኪናቸው አወጥተው ብሩን ሊመነዝሩ ሲሉ በባንኩ ጥቆማ መሰረት በተደረገ በክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ተገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ የፋይንስና ንግድ ነክ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ እንደገለጹት፥ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ጋር በተደረገ ክትትል ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ከዚያም ባለፈ በቱሉ ዲምቱ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ ተመሳሳይ መጠን ያለው ሃሰተኛ ብር መያዙን ረዳት ኮሚሸነት ብርሃኑ ተናገረዋል። በአሁኑ ወቅት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛልም ነው ያሉት።

ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አያይዘውም ባንኮችም ሆኑ ህብረተሰቡ ከአዲሱ ብር ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ማንኛውንም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጠጥ እንዲሁም በገጠር አካባቢዎች ህገ ወጥ ግለሰቦች በሐሰተኛ የብር ኖቶች የተለያዩ ግዢዎችን ሊፈጽሙ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ አሮጌውን ገንዘብ የሚቀበል ከሆነ የጊዜ ሰሌዳው ያላለፈበትና ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ ቤቱን ለተከራዮች በሚያከራይበት ጊዜ ስለ ተከራዮቹ በሚገባ አውቆ ማከራየት እንዳለበት እንዲሁም በተከራዩዋቸው ቤቶች ውስጥ ምን እንደሚሰሩና ከማን ጋር እንደሚውሉ በንቃት መከታተል አለበት ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳን ስራው አሰልቺና አድካሚ ብሆንም የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ህገ ወጥ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍና የወንጀል ምርመራ ቢሮ አባላትን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ላደረጉት ብርቱ ክትትል ምስጋናቸውን ያቀረቡት ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ በህገ ወጦች ዙሪያ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
(ምንጭ – የፌደራል ፖሊስ)