ኢትዮጵያ እና ብሪታንያ የ115 ሚሊየን ፓውንድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

ኢትዮጵያ እና ብሪታንያ የ115 ሚሊየን ፓውንድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

Amharic

ኢትዮጵያ እና ብሪታንያ የ115 ሚሊየን ፓውንድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። ስምምነቱን የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ እና የብሪታንያ ዓለም አቀፍ የልማት ሚኒስትር ፔኒ ሞርዳውንት ተፈራርመውታል።

በስምምነቱ መሰረት 35 ሚሊየን ፓውንዱ የኢትዮጵያን የግብር አሰባሰብ ስርዓት ለማሻሻል የሚጀመረው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ነው።

80 ሚሊየን ፓውንዱ ደግሞ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ስራ ፈጠራ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ይውላል ተብሏል።

ፕሮግራሙ በእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዲ ኤፍ አይ ዲ) የሚተገበር ይሆናል።

የግብር አሰባሰብ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ የኢትዮጵያን የግብር አሰባሰብ ስርዓት በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል።

ይህም የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በማጠናከር ሃገሪቱ የምታካሂደውን የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም በራስ አቅም ለመሸፈን ያስችላል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም ኢንቨስትመንትን እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ያግዛልም ነው የተባለው።

የተቸገሩ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ የሚገኙ 30 ሺህ ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የስራ ፈጠራ ፕሮግራም ደግሞ፥ የተጠቃሚዎቹን ህይዎት በመቀየር ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

ሚኒስትሯ ዛሬ ረፋድ ላይ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጋር በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና በድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ላይ በማድረግ ተወያይተዋል።

ከዚህ ባለፈም በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚገኘውን የእንግሊዝ ጨርቃ ጨርቅ አምራች ፋብሪካን ጎብኘተዋል።

እንዲሁም የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት በሃዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለሚገኙ ሰራተኞች ደህንነትና ዋስትና የሚያደርገውን የ3 ሚሊየን ፓውንድ ድጋፍም ይፋ አድርገዋል።

(በኤፍ ቢ ሲ)