ፓርላማው የ2011 ረቂቅ በጀት ላይ ተወያየ

ፓርላማው የ2011 ረቂቅ በጀት ላይ ተወያየ

የአማርኛ-ወሬዎች

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት እየተካሄደ ባለው መደበኛ ስብሰባው በቀረበለት የ2011 346 ቢሊየን 915 ሚሊየን 451 ሺህ 948 ብር ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ተወያየ።

በውይይቱ ላይም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን፥ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም ተከስተ ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ሰጥተዋል።

ዶክተር አብረሃም ተከስተ በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያም፥ የፌደራል መንግስት መደበኛ በጀት እና የካፒታል ወጪ በጀት ላይ በ2011 ረቂቀ በጀት ቅናሽ መደረጉን አስታውቀዋል።

በ2011 ረቂቀ በጀት የተቀመጠው የፌደራል መንግስት መደበኛ በጀት ከ2010 በጀት ጋር ሲነፃፀር በ4 በመቶ ቅናሽ አንዳለው አስታውቀዋል።

የካፒታል ወጪ ረቂቅ በጀት ደግሞ ከ2010 በጀት ጋር ሲነፃፀር የ1 በመቶ ቅናሽ አለ ያሉት ዶክተር አብረሀም፥ የፌደራል መንግስት መደበኛ በጀት እና የካፒታል ወጪ ላይ በድምሩ የ2 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ መደረጉን አስታውቀዋል።

ዶክተር አብረሃም የ2011 የመደበኛ ወጪ ረቂቅ በጀትን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም ለ2011 ለመደበኛ ወጪ የተያዘው በጀት ዝቅ ደረጉንም አስታውቀዋል።

የ2011 የመደበኛ ወጪ ረቂቅ በጀት ከ2010 በጀት ጋር ሲነፃፀር በ4 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉንም አስታውቀዋል።

የፌደራል መንግስት መደበኛ በጀት እና የካፒታል ወጪ ላይ ቅናሽ የተደረገው ደግሞ የገቢ አቅም ማነስ ምክንያት ነው ብለዋል ዶክተር አብረሃም።

መንግስት በ2011 በጀት ዓመት የያዛቸውን እቅዶች ለመተግበር ገቢ መሰብሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር አብረሃም ገለፃ፥ በ2011 በጀት ዓመት ታክስ የመሰብሰብ አቅምን ማሻሻል ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ለክልሎች የሚሰጠውን ድጋፍ አስመልክቶም በ2011 ረቂቅ በጀት ለክልሎች የሚሰጠው ድጋፍ ከፍ እንዲል መደረጉንም ዶክተር አብረሃም አስታውቀዋል።

በ2011 ረቂቅ በጀት ለክልሉች የሚደረግ ድጋፍ ከ2010 በጀት ጋር ሲነፃፀር በ16 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን ገልፀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው እለት በሚያካሂደው ልዩ ስብሰባው ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በረቂቅ በጀቱ ላይ ተወያይቶ ያፀድቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2011 ዓ.ም በጀት 346 ቢሊየን 915 ሚሊየን 451 ሺህ 948 ብር እንዲሆን ወስኖ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩ ይታወቃል።

ምክር ቤቱም ለዝርዝር እይታ ረቂቅ በጀቱን ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶ ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል።

ከዚህ ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 91 ቢሊየን 67 ሚሊየን 160 ሺህ 588 ብር እንዲሁም 113 ቢሊየን 635 ሚሊየን 559 ሺህ 980 ብር ደግሞ ለካፒታል ወጪ የተመደበ ነው።

ከዚህ ባለፈም 135 ቢሊየን 604 ሚሊየን 731 ሺህ 380 ብር ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ደግሞ 6 ቢሊየን ብር ተመድባል።

(በኤፍ.ቢ.ሲ)