ጎበዝ ሌቦች እየተጫወቱብን ነው!!

ጎበዝ ሌቦች እየተጫወቱብን ነው!!

አስተያየት

በመላኩ ብርሃኑ – ይቺ ሃገር ሜጋ ፕሮጀክት ‘አይውጣልሽ’ ተብላ የተረገመች ይመስል ፕሮጀክቶቻችን በሙሉ ሳንካ ኣላጣቸው ብሏል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአምስት አመት ይጠናቀቃል ቢባልም ይኸው ዛሬ ድረስ በኤሊ ጉዞ እያዘገመ ይገኛል።

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ለምን አላጠናቀቀውም ብሎ የጠየቀ ማንም የለም። መቼ እንደሚጠናቀቅም የሚያውቅ ማንም የለም። ብቻ ግንባታው የደረሰበት ደረጃ በፐርሰንት እየተነገረ አሁንም ቀጥሏል።

ከዚህ በባሰም የግድቡ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራ ኮንትራት የወሰደው ሚቴክ ከገነባቸው ተርባይኖች ውስጥ አንዳቸውም አለመስራታቸው አጠያያቂ ሆኗል። ጭራሽ ሳሊኒ በዚህ ችግር ምክንያት ግንባታ ማካሄድ ባለመቻሌ ለባከነው ጊዜ ክፍያ ይሰጠኝ ብሎ የሚሊዮን ዶላሮች ጥያቄ ማቅረቡ እየተነገረ ነው። ያለን አንድ ብሄራዊ ኩራት ይኸው ግድባችን ነው ብለን ተስፋ ብንጥል ጭራሽ ስንክሳሩን እያበዙብን ነው።

እዚህ ጋ ደግሞ የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈጻጸም አስቂኝ ሆኗል። በሁለት አመታት ይጠናቀቃል የተባለው ይኼ የቢሊዮን ብሮች ፕሮጀክት አራት አመት ድረስ ሲጓተት ትዝ ያለውም ሰው አልነበረም። ሚዲያዎቻችንም ለምን ብለው አልጠየቁም። የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴም እንደተቆጣጣሪ አካልነቱ ጉዳዩ ሲከነክነው አላስተዋልንም።

እንዲያም ሆኖ አራት አመት ፈጅቶ ሰሞኑን ተጠናቀቀ ተብሎ በፕሬዚዳንቱ መመረቁ በራሱ አስቂኝ ነገር ወልዷል። ጣቢያው ይህ ሁሉ ወጪ የወጣበት 50 ሜጋዋት እንዲያመነጭ ቢሆንም ኮንትራክተሩ ብሩን እንክት አድርጎ በልቶ የገነባው ፕላንት ማመንጨት የቻለው 25 ሜጋዋት ብቻ ነው።

በአካሄዱ መሰረት ድርጅቱ የገባውን ውለታ መፈጸም ባለመቻሉ የኢትዮጵያ መንግስት ፕሮጀክቱን መረከብ አልነበረበትም። የሆነው ግን በተቃራኒው ነው። ጭራሽ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሄር በተገኙበት ተመርቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አዜብ “ግንባታው በውላችን መሰረት ስላልተከናወነ ድርጅቱን እንከስሳለን” ያሉት ዛሬ ነው። ድርጅቱ ጨረስኩ ብሎ ለምረቃ እስኪያበቃው ድረስ የሚመሩት ተቋም የት ነበር ለሚለው ጥያቄ በበኩሌ መልስ የሚሰጠኝ አላገኘሁም።

ነገሩ ጅብ ከሄደ …አይነት ይመስላል። ብሩ ተበልቷል። ድርጅቱን በአለም አቀፍ ህግ ለመክሰስ ያለው ውጣ ውረድና የኢትዮጵያን ተከራክሮ የመርታት ባህል ስናየው ግን ውጤት የማግኘቱ ነገር በጣም ተስፋ ያስቆርጣል። በእውነቱ ይህ ግዙፍ ኪሳራ ነው።

ወዲህ በሃገር ውስጥ አቅም ይገነባሉ ያልናቸው የስኳር ፕሮጀክቶቻችን 77 ቢሊዮን ብር ቅርጥፍ አድርገው በልተው ውሃ ላይ ጥለውናል። ለዚህ ሁሉ ክስረት የሚከስስም የሚከሰስም ወገን አላየንም። ገንዘባችን አንዴ ከወጣ በኋላ ምናልባት የሆነ ቀን ላይ የት ገባ ብሎ የሚጠይቅ አፈቀላጤ እንጂ ከገባበት ጉድጓድ መዝዞ የሚመልስ ሃይል ግን ገና አላፈራንም። ህግ እንጂ ሰይፍ የለንም። ካለንም ህጋችን ለቃሪያ ስርቆት አምስት አመት የሚቀጣ፣ ለሃገር ሃብት ስርቆት ግን አይኑን የሚጨፍን ህግ ሆኖብናል።

ሲጀመር ይህቺ ሃገር በኮንትራት አስተዳደር በኩል ትልቅ የባለሙያ እጥረት አለባት። በተለይ ለውጭ ኩባንያዎች የሚሰጡ ፕሮጀክቶች ሁሌም ሃገሪቱን ሲጎዱ እንጂ ሲጠቅሙ ታይቶ አይታወቅም። ኢትዮጵያ ተጎድታም ከሳሽ ሆና ስትቀርብ ጥሩ አለምአቀፍ ጠበቃ ስለሌላት አንጀት አርስ ፍትህ አግኝታ አታውቅም። እዚህ ጋ ከእጃችን ያመለጠውን ጤፋችንን ጉዳይ ማስታወስ ይቻላል።

ምን እየተካሄደ ነው? በደሃ አቅማችን ተንቆጣቁጠን የምናወጣት ብር የት እየገባች ነው? የውስጡም ቦጥቧጭ፣ የውጪውም ቦጥቧጭ የሆነብን ማን ቢረግመን ነው? ሁሉም ሌባ የሆነብን ኪሳችንን ክፍት ትተን ይሆን ወይስ ሌቦችን የሚቀጥረው ተቋማችን የሌቦች አለቃ ስለሆነብን ? ….ያሳዝናል!!