የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለጫ የ2011 አዲስ ዓመት አስምልክቶ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለጫ የ2011 አዲስ ዓመት አስምልክቶ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለጫ የ2011 አዲስ ዓመት አስምልክቶ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቻይና እና የኤርትራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ ቆይታቸውን አና መጪዉን አዲስ ዓመት አስምልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

አዲሱን ዓመት አስመለክተው ባስተላለፉት መልእክት፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለ2011 አዲስ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁ ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት ተባብረን ከሰራን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም ትልቅ እድል የሚፈጠርበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመጪው ዓመት ከዚህ ቀደም ስንከተለው የነበረውን አካሄድ ትንሽ ለወጥ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።

ከዚህ ቀደም በአዲስ ዓመት ጭፈራዎች ላይ እንዳለው “ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ እንጨት ሰብሬ ቤት እስከሰራ” የሚለው አሁን አይሰራም፤ ቆሞ ማየት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ባለእንጀራ በጉልበቱ ልክ እንጨት እያነሳ ሁሉም የበኩሉን የሚጠዋበት አካሄድ ካልተከተልን፤ አንዱ እየሰራ ሌላው ቆሞ የሚያይ ከሆነ የሚፈለገውን ልማትና እድገት ልናመጣ እንችልም ብለዋል።

ስለዚህ የዘንድሮ የአዲስ ዓመት ጭፈራዎቻችን “ባልንጀሮቼ ቁሙ በተራ ሳይሆን፤ ባልንጀሮቹ አብረን እንስራ” እንደሚሆን እምነት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።

“እንኳን ቤትና የለኝም አጥር” የሚለው እሳቤም ሊቀየር ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ቤት ብቻ ሳይሆን ድንቅ ቤት ኢትዮጵያ የተባለች ቤት ሁላችንም ስላለን፤ ሁላችንም በጋራ ልንሰራ እና ልንቆም ይገባል ብለዋል።

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በአዲሱ ዓመት በሀገራቸው ልማት እና ግንባታ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።

በአዲሱ ዓመት ተባብረን እና ተጋግዘን ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንደምንመልስ ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉም ተናግረዋል።

በመግለጫቸውም በቻይና እና በኤርትራ የነበራቸው ቆይታ ስኬታማ እንደነበረ አንስተዋል። በቻይና ቆይታቸውም በቻይና አፍሪካ ፎረም ላይ በመሳተፍም የኢትዮጵያን ሚና እንደ ሀገር እንደ አህጉር ለማጉላት መቻሉን ገልፀዋል።

እንዲሁም ከፎረሙ ጎን ለጉን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እና የቻይና መንግስት መሪዎች ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

ከቻይና መሪዎች ጋር በነበራቸው ቆይታም በተለይም ከብድር ጋር በተያያዘ በ10 ዓመት ይከፈል የነበረው የኢትዮ ጂቡቱ ባቡር መስመር ግንባታ ብደር ወደ 30 ዓመት ከፍ እንዲል መደረግ መቻሉን አንስተዋል።

በሌሎች የብድር አሰጣጠቶች ላይም ማሻሻያዎቸን ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን እና መስማማታቸውን ገልፀዋል።

ወደ ኤርትራ ያቀኑበት ዋነኛ ምክንያትን ሲገልጹም፥ ሁለቱ ሀገራት የደረሱት ስምምነት ወደ ተግባር መሸጋገሩን እና መሬት መውረዱን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።

በኤርትራ ቆይታቸውም ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል ዝግጅት ላይ መሆኗን ገምግመናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ወደቡ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምርም አስረድተዋል።

በምፅዋ በነበራቸው ቆይታም አንድ የኢትዮጵያ መርከብ ወደ ኤርትራ ምፅዋ ወደብ በመምጣት እቃ መጫኗን አንስተው፤ ይህ መጀመሩም ሀገራቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ያጡትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች መልሶ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ኤርትራ ከፍተኛ የሆነ የአሳ ምርት አላት፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አሳ የምታስገባው ከሩቅ ሀገራት ነው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በመጀመሩ ግን በቀላሉ ከኤርትራ በማስገባት እና የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ወደ ኤርትራ በመላክ በአነስተኛ የውጭ ምንዛሬ የንግድ ልውውጥ ልናደርግ ያስችለናልም ብለዋል።

በኤርትራ የተከፈተውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስመልክቶም፥ ኤምባሲው በኤርትራ እንዲከፈት ከፍተኛ እገዛ ላደረገው የኤርትራ መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኤምባሲው የተከፈተው ከዚህ በፊት አንድ የኤርትራ የሚኒስትር መስሪያ ቤት የነበረ ህንፃ ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ህንፃውም በአስመራ አሉ ከሚባሉት ውስጥ ተመርጦ ነው ብለዋል።

ይህ የሚያመላክተውም ኤርትራ ለኢትዮጵያ ያላትን አክብሮት ነው፤ በዚህም ደስ ብሎናል፤ ምስጋናችንንም ልናቀርብ እንፈልጋለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አክለውም በኤርትራ የነበራቸው ቆይታ ከኢትዮ ኤርትራ በተጨማሪም የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የሶስትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር ያስቻለ እንደነበረም ገልፀዋል።

ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከፕሬዚዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ጋር በነበራቸው ቆይታም የሶስቱን ሀገራት ህዘቦች የበለጠ ለማቀራረብ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውንም አንስተዋል።

እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን ከጦርነት እርስ በእስር መጠፋፋት በማላቀቅ ሰላማዊ ቀጠና ለማድረግም ተስማምተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ በዛሬው እለትም አንድ ትልቅ ልኡክ ወደ ጂቡቲ መላኩንም አንስተዋል።

ልኡካኑም ኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ያካተተ ሲሆን፥ በተለይም በኤርትራ እና በጂቡቲ መካከል ባለው የድንበር አለመግባባትን መፍታት በሚቻልበት ላይ እንደሚመክርም አንስተዋል።

ቀጠናው ከጦርነት ቀጠና ተላቆ የሰላም ቀጠና እንዲሆን እንፈልጋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ይህ መሆን ከቻለ በቀጠናው ትልቅ አቅም ስላለ የገበያ ትስስር በመፍጠር ብቻ የሌሎችን እጅ ሳናይ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።

(በኤፍ ቢ ሲ)